ዳታዎቻችንን የክላውድ ማከማቻ አገልግሎት (cloud storage service) ላይ የማስቀመጥ በርካታ ጥቅም! 

የስልክ፣ የላፕቶፕ፣ የታብሌት እንዲሁም የሌሎች ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መሰረቅ እና መጥፋት በማህበራዊ ሚዲያ በየዕለቱ ከምንሰማቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል። ብዙ ግዜ እቃዎቹን የተሰረቁ ግለሰቦች የስልኩ ወይንም የላፕቶፑ መጥፋት ሳይሆን በውስጡ የተከማቹ ዳታዎች በሌላ ሰው ዕጅ መግባታቸው በተለይ እንደሚያሳስባቸውም ሲናገሩ ይደመጣል። 

በእርግጥ ለብዙ ዓመታት ያከማቸናቸው ፎቶዎች፣ የስልክ አድራሻዎች፣ ጽሁፎች፣ እና ሌሎች ዳታዎች ከዕጅ ሲወጡ በግልና በስራ ህይዎታችን ላይ ብዙ ነገር ያመሰቃቅላሉ። 

በስርቆትም ይሁን በመጥፋት አልያም በብልሽት ምክንያት በስልክዎት ወይንም በላፕቶፕዎ ያከማቿቸው ዳታዎች ከእጅዎ ወጥተው እንዳይቀሩ የክላውድ ማከማቻ አገልግሎት (cloud storage service) መጠቀም ይመከራል። 

የክላውድ አገልግሎት ፎቶዎች፣ የስልክ አድራሻዎች፣ ፋይሎችና ሌሎች ዳታዎችን በማከማቸት በስልክዎ ወይንም በላፕቶፕዎ እንዳይቀመጡ ያስችልዎታል። ጎግል፣ አፕል፣ ድሮፕቦክስ፣ ማይክሮሶፍት እና ሌሎች ድርጅቶች የክላውድ አገልግሎት የሚያቀርቡ ሲሆን ዋን ድራይቭ (One Drive)፣ ጎግል ድራይቭ (Google Drive)፣ ድሮፕቦክስ (Dropbox) እና አይክላዎድ (iCloud) ከተለመዱ መተግበሪያዎች መካከል ይጠቀሳሉ። 

ብዙዎቹ የክላውድ አከማች መተግበሪያዎች አዲስ ስልክ ወይንም ላፕቶፕ ሲገዙ አብረው ተጭነው የሚመጡ ሲሆን ከሌሉ በቀላሉ አውርደው መጫን ይችላሉ። ለምሳሌ አንድሮይድ ስልክ ካለዎት የጎግል ድራይቭ መተግበሪያን በቀላሉ በመጠቀም ፋይልዎችዎን ማከማቸት የሚችሉ ሲሆን የሚያስፈልግዎ የጂሜይል አካውንት መክፈት ብቻ ይሆናል። ጎግል ድራይቭ 15 ጂጋ ባይት ነጻ ማከማቻ ይሰጥዎታል።  

ፋይልዎችዎን በክላውድ ማከማቸት ከጀመሩ በኃላ ስልክዎ አልያም ላፕቶፕዎ ቢሰረቅ፣ ቢጠፋ አልያም ቢበላሽ ሌላ ስልክ ወይንም ላፕቶፕ በመጠቀም እንደገና ማግኘት ይችላሉ። የክላውድ ማከማቻ አገልግሎት የፋይሎችን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በስልክዎና በላፕቶፕዎ የሚያከማቿቸውን ዳታዎች እንዲቀንሱ ያስችልዎታል። 

ከፕራይቬሲና ከሌሎች የዳታ ደህንነት ጉዳዮች አንጻር ፋይሎችን በክላውድ መተግበሪያዎች ማስቀመጥን በተመለከት የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉ ሲሆን ብዙዎቹ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ባለስ ሶስት ደርዝ ስወራን (three levels of encryption) በመጠቀም የዳታዎችን ደህንነት ይጠብቃሉ። 

በክላውድ ማከማቻ የሚቀመጡ ፋይልዎችዎን ደህንነት ይበልጥ ለመጠበቅ ጠንካራ የማለፊያ ቃል (password) መጠቀም፣ የማለፊያ ቃል በየጊዜ መቀየር እና ለተለያዩ አካውንቶች ልዩ የሆኑ የማለፊያ ቃሎችን መጠቀም ይመከራል። የይለፍ ቃል የሚያስተናብሩ (password manager) መገልገያዎች እንዲሁም ባለሁለት ደርዝ ማረጋገጫ (two-step verification) መጠቀምም ጥሩ ነው። አጠራጣሪ ኢሜሎችን አለመክፈትም እንዲሁ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::