አስረኛው ዓለም አቀፍ የሚዲያ እና የመረጃ አጠቃቀም ንቃት (Media and Information Literacy) ሳምንት!

አስረኛው ዓለም አቀፍ የሚዲያ እና የመረጃ አጠቃቀም ንቃት (Media and Information Literacy) ሳምንት ከጥቅምት 14-21 2014 ዓ.ም “የሚዲያ እና የመረጃ አጠቃቀም ንቃት ለማህበረሰብ ጥቅም” በሚል መሪ ቃል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ እና ምርምር ተቋም (ዩኔስኮ) አዘጋጅነት በመከበር ላይ ይገኛል።

የሚዲያ እና የመረጃ አጠቃቀም ንቃት ዜጎች መረጃ ከማግኘት እስከ መረጃ አጋሪነት ያላቸውን ተሳታፎ የሚያጠቃልል ሲሆን በሂደቱም መረጃ ማሰስን፣ በጥንቃቄ መገምገምን እና መጠቀምን ይመለከታል። በተጨማሪም ዜጎች መረጃ ከማግኘት እስከ መረጃ ማጋራት ባሉት ሂደቶች የሚኖራቸውን መብቶችና ግዴታዎች እንዲሁም ስነ-ምግባር ያካትታል።

የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ዜጎች ስለመረጃና መረጃውን ስለሚያሰራጩ ሚዲያዎች ምንነትና ማንነት ያላቸውን እውቀት ከፍ በማድረግ ከተቀባይነት ወደ ንቁ ተሳታፊነት ያሳድጋቸዋል። በዚህም ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን እንዲሁም ጥላቻን ያካተቱ ዘገባዎችን በቀላሉ እንዲለዩና በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ በማስቻል ጤነኛ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበረሰባዊ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር ያስችላል።

በኢትዮጵያ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት በዝቅተኛ ደረጃ እንደሚገኝ የሚገመት ሲሆን ይህም ለሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም በጥላቻ ለተለወሱ ዝገባዎች ስርጭት ከፍ ያለ አስተዋጾ ይኖረዋል። ዝቅተኛ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ባለባቸው ሀገሮች መረጃን የማመንጨትና የማሰራጨት ይዞታ በልሂቃንና በጥቂት ቡድኖች ስር እንዲሆን በማድረግ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ተመልካች፣ ተቀባይና በተጽኖ ስር የወደቀ እንዲሆን ያደርጋል። ይህም የነቃና ጠያቂ ብዙሃን እንዳይኖር በማድረግ ለግጭትና ለማህበረሰባዊ ምስቅልቅሎሽ በር ይከፍታል።

በአንጻሩ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ከፍ ያለ ደረጃ በደረሰባቸው ሀገሮች ዜጎች መረጃን ከማግኘት እስከ መረጃን ማምረት የነቃ ተሳትፎ ስለሚኖራቸው ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭት በቀላሉ የመጋለጥ ዕድላቸው ያነሰ ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::