የፈጣን መልዕክት መለዋወጫ አገልግሎት የሚሰጠው ቴሌግራም አዳዲስ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታውቋል!

ከማሻሻያዎቹ መካከል በቴሌግራም ግሩፖች ማንነትን ሳይገልጹ መልዕክት ማስተላለፍና ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ፣ ከቻናልና ከግሩፕ አባላት ውጭ የሆኑ ሰዎች ይዘቶችን ‘ሴቭ’ እንዳያደርጉ የሚከለክሉ እንዲሁም ይዘቶችን ማጥፋት የሚያስችሉ ይገኙባቸዋል።

በአዲሱ ማሻሻያ የቴሌግራም ግሩፕ አባል የሆነ ግለሰብ ማንነቱን ሳይገልጽ መልዕክት ማጋራት ወይንም ምላሽ መስጠት ከፈለገ ማስተላለፍ ከፈለገው መልዕክት ጎን የሚታየውን የፕሮፋይል ምስል በመጫን ፍላጎቱን ማስተካከል ያስችለዋል። የሚያጋራው መልዕክት ወይንም ምላሽም አባል በሆነበት የቴሌግራም ግሩፕ ስምና ፕሮፋይል ምስል የሚወጣ ይሆናል።

ሌላኛው በአዲሱ ማሻሻያ የተካተተው የቴሌግራም ቻናል ወይንም ግሩፕ ባለቤቶችና አስተዳዳሪዎች በቻናላቸው ወይንም በግሩፓቸው የሚጋሩ መልዕክቶችን ተደራሽነት እንዲወስኑ የሚያስችላቸው ነው። በዚህ ማሻሻያ የቻናል ወይንም የግሩፕ ባለቤቶችና አስተዳዳሪዎች በቻናላቸው ወይንም በግሩፓቸው የሚጋሩ ይዘቶች ታዳሚዎችን ማንነት መወስን የሚችሉ ሲሆን ከተፈቀደላቸው ታዳሚዎች ውጭ ወደ ሆኑ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች መልዕክቶችን ማስተላለፍ (message forwarding)፣ የስክሪን ቅጅ (screenshot) መውሰድ እንዲሁም ‘ሴቭ’ ማድረግን ይከለክላል።

እንዲሁም አዲሱ የቴሌግራም ማሻሻያ ተጠቃሚዎች ከግለሰቦች ጋር የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች (chat history) መሰረዝ እንዲችሉ የሚረዳ ሲሆን ተጠቃሚዎች የሚሰርዟቸውን መልዕክቶች የመምረጥ ዕድልም ይሰጣል።

በተጨማሪም በአዲሱ ማሻሻያ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች ወደ አካውንታቸው በተመሳሳይ ጊዜ ከአንድ በላይ በሆኑ ስልኮች፣ ላፕቶፖች ወይንም ሌሎች መገልገያዎች መግባት (login) የሚችሉ ሲሆን ከዴስክቶፕ ኮፒዩተሮች ጋር ማገናኘት ይችላሉ። ይህም የአካውንታቸውን ደህንነት የበለጠ ለመቆጣጠር ያስችላቸዋል የተባለ ሲሆን በአንድ ጊዜም መውጣት (logout) እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

ቴሌግራም ሌሎች በርካታ ማሻሻያዎችንም ያደረግ ሲሆን ማሻሻያዎቹ የተጠቃሚዎችን ደህንነት የበለጠ ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን ገልጿል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::