ከትላንት ጀምሮ በርካታ የፌስቡክ ገጾችና አካዉንቶች በሀላባ ዞን አንዳንድ አካባቢዎችና በወራቤ ከተማ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃት መፈጸሙን መረጃዎች እያጋሩ ይገኛሉ! 

የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም መረጃዉን እንድናጣራ ጠይቀዉናል።

በዚሁም መሰረት ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ የሀላባ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ መሃመድ ከድር እና የወራቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊልን አናግሯል። 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስትን መግለጫም ተመልክቷል። 

“በሀላባ ዞን አንዳንድ አከባብቢዎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል” በማለት የተሰራጨዉ መረጃ ሀሰት መሆኑን የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ መሃመድ ከድር  ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል። 

“በጣም የተሳሳተ መረጃ ነዉ። የሀላባ ህዝብ ሙስሊሙና ኦርቶዶክሱ አንዱ እምነት የአንዱን እምነት የሚገነባ፤ ለችግሩ ደራሽ የተጋመደ ህብረተሰብ ነዉ” ሲሉም ቤተክርስትያን ተቃጥሏል በማለት የተሰራጨዉ መረጃ ትክክል እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል በትላንትናዉ እለት በከተማዉ የሚገኘዉ ቅ/ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት መፈጸሙን ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጠዋል።

“ችግሩ ተፈጥሯል፤ ለማረጋጋት ሞክረን ሰዉን አረጋግተነዉም ነበር። ግን ከዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎች ናቸዉ ‘ማኔጅ’ እንዳይደረግ ከቁጥጥር ዉጭ እንዲሆን ያደረጉት። በዛ መነሻ ችግሩ ተፈጥሯል፤ ቤተክርስቲያን ተቃጥሏል” ብለዋል።

ጥፋተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ያሲን ከሊል ነግረዉናል። 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዛሬዉ እለት ባወጣዉ መግለጫ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ‘በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አብያተ ክርስትያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈጸመዉን ህገ ወጥና የወንጀል ተግባር’ አዉግዟል። 

 

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልም ትላንት ሚያዚያ 20/2014 ዓም በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ እና ሳንኩራ ወረዳ በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ዛሬ በወጣዉ መግለጫ አረጋግጧል። የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንደሚሰራም የክልሉ መንግስት በመግለጫዉ አስፍሯል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::