የሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አሰራጭተዋል የተባሉ ስድስት መገናኛ ብዙኃን በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው! 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አሰራጭተዋል ባላቸው ስድስት መገናኛ ብዙኃን ላይ ምርመራ እንዲካሄድባቸው ሰነዶች አደራጅቶ ለፌደራል ፖሊስ መላኩን አስታወቀ። ባለሥልጣኑ ምዝገባ ሳያከናውኑ በበይነ መረብ አማካኝነት በህገወጥ መልክ የሚዲያ ስርጭት ላይ የተሰማሩ 25 ድርጅቶችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሂደት መጀመሩንም ገልጿል። 

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ አርብ ሚያዝያ 21፤ 2014 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳሉት፤ መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ዘጠኝ ወር ባከናወነው የሞኒተሪንግ ስራ በስድስት መገናኛ ብዙሃን በተሰራጩ 10 ፕሮግራሞች ላይ የህግ ጥሰቶች ተስተውለዋል።  

“ከሐሰተኛ [መረጃ] እና ጥላቻ [ንግግር] ጋር ተያይዞ አስር ፕሮግራሞች ላይ የህግ ጥሰት በመስተዋሉ ፋይሉን አደራጅተን ለህግ አስፈጻሚ አካላት፣ ለፌደራል ፖሊስ ጥቆማ አቅርበናል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህግ አስፈጻሚ አካላት በሚያደርጓቸው ምርመራዎች ላይ የተቋሙን ሙያዊ ድጋፍ በሚፈልጉበት [ጊዜ] ሁሉንም የጠየቁትን ጥያቄ በህጉ እና በህጉ ብቻ መሰረት አድርገን ሙያዊ ድጋፍ ሰጥተናል” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል። 

አቶ መሐመድ የመገናኛ ብዙኃኑን ማንነት በስም ከመጥቀስ ቢቆጠቡም፤ በንግድ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የተሰማሩ እንደሆኑ ግን በሪፖርታቸው ላይ አመልክተዋል። እነዚህ መገናኛ ብዙኃን “ሚዛናዊነት የጎደላቸው እና የአንድ ወገን ሀሳብና ፍላጎትን የሚያንጸባርቁ አድሏዊ ዘገባዎችን በማቅረብ” የህግ ጥሰቶችን መፈጸማቸውንም ጠቁመዋል። 

Source: Ethiopia Insider

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::