በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ስራ እናስቀጥራችኋለን በማለት ከሚያጭበረብሩ አካላት ህዝቡ እንዲጠነቀቅ ተቋሙ አሳስቧል

የተለያዩ የማደናገሪያ መንገዶችን በመከተል ከስራ ፈላጊው ገንዘብ በመቀበልና በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ስራ እናስቀጥራለን በማለት የማጭበርበር ድርጊት እየፈጸሙ የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች መኖራቸውን በጥቆማ እንደደረሰበት ተቋሙ በትናንትናው ዕለት ባወጣው የጥንቃቄ መልዕክት ገልጿል። 

ከእንዲህ ያሉ የማጭበርበር ድርጊቶች ህዝቡ እራሱን እንዲጠብቅ ያሳሰበው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ምንም አይነት አዲስ የስራ ቅጥር ያላከናወነ መሆኑን አስታውቋል። 

ተቋሙ ጨምሮ እንደገለጸው “የሰራተኛ ቅጥር የሚፈጸመው ተገቢውን ህግና ስርዐት ተከትሎ በግልጽ ህዝባዊ ማስታወቂያዎችን አስነግሮ መሆኑን” አብራርቷል። በጥንቃቄ መልዕክቱ ተቋሙ የሚከተላቸው የቅጥር ሂደቶችም ተገልጸዋል። 

የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ህብረተሰቡ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ሲመለከት በተቋሙ ነጻ የስልክ መስመር 8561 ወይም በ011-551-7184 ጥቆማ እንዲያደርስ ጥሪ አቅርቧል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::