የሩሲያ ዶክተሮች የኮቪድ-19 በሽታ መነሻ ቫይረስ ሳይሆን ባክቴሪያ መሆኑን ደረሱበት” በሚል የተሰራጨው መረጃ ምን ያህል እውነት ነው? 

“የሩሲያ ዶክተሮች የኮቪድ-19 በሽታ የሚመጣው ከቫይረስ ሳይሆን ከባክቴሪያ እንደሆነ ደርሰውበታል፣ በሽታውም በአንቲባዮቲክ እና አስፕሪን ሊታከም እንደሚችል ገልፀዋል፣ ዶክተሮቹ [ይህን ምርምር ለማድረግ] በኮቪድ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች የአስከሬን ምርመራን የአለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ህግ በጣሰ መልኩ ነው ያደረግነውም ብለዋል” የሚል መረጃ በስፋት እየተጋራ ይገኛል፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድም በዋትስአፕ እና በሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገፆች እየተሰራጨ ይገኛል። 

ይህን ተከትሎ አሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) እና ሬውተርስ መረጃውን አጣርተው ዘገባ ሰርተዋል። 

ኤፒ ይህ መረጃ የሀሰት እንደሆነ በዘገባው አብራርቷል። የኮቪድ-19 በሽታ የሚመጣው ከቫይረስ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር እንደሌለው እና የተጠቀሱት መድሃኒቶች ኮቪድን ለመከላከል ውጤታማ እንዳልሆኑ የሚጠቅሰው ይህ ዘገባ የአለም የጤና ድርጅትም በኮቪድ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን አስከሬን መመርመርንም አይከለክልም በማለት ይገልጻል፣ እንዲያውም እነዚህ ምርመራዎች እንዴት ሊደረጉ እንደሚገባ አጋዥ ምክሮችን እንደሚያቀርብ ያትታል።

(የአሶሺዬትድ ፕሬስን ሙሉ ዜና ለማንበብ፡ https://apnews.com/article/fact-checking-afs:Content:10056037732) 

በሌላ በኩል ሬውተርስ “ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት እንደማይሞቱ እና ይልቁንም ቫይረሱ በሚያመጣው እብጠት እና የደም መርጋት መሆኑ ታውቋል፣ የ5G ቴክኖሎጂም በሽታውን ያስከትላል” ተብሎ እየተሰራጨ ያለ መረጃ ትክክል እንዳልሆነ ከሰፊ ትንታኔ ጋር አቅርቧል። ሌላው ሬውተርስ ያጋለጠው የሀሰት መረጃ “እስካሁን ሩስያ ውስጥ በኮቪድ-19 በሽታ ተጠቅቶ የከፍተኛ እንክብካቤ ክፍል (ICU) እና ለመተንፈስ የሚረዱ መሳሪያዎችን (ventilators) የተጠቀመ ሰው የለም” መባሉን ነው። የዜና አውታሩ በሩሲያ ውስጥ እነዚህን መሳሪያዎችም ሆነ የከፍተኛ እንክብካቤ ክፍል ውስጥ የገቡ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ እና አሁንም እንዳሉ አረጋግጦ ፅፏል። 

(የሬውተርስን ሙሉ ዜና ለማንበብ: https://www.reuters.com/article/factcheck-russia-covid-autopsy-idUSL1N2M82C9)

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::