በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ ቼክ ያቀረቡት ቅሬታ እና ሆስፒታሉ ያደረሰን መልስ!

በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ከሰሞኑ ወጣ ባሉት የሆስፒታሉ አስተዳደር አዲስ መመሪያ ላይ ቅሬታቸዉን አድርሰውናል።

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ “አንድ ባለሙያ መስራት ከሚጠበቅበት ሰዓት በላይ እንድንሰራ እየተገደድን ነዉ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠዉን የወረርሽኝ የስራ ሰዓት በሚጣረስ መልኩ ለተከታታይ ስምንት ሰዓታት ያለእረፍት፣ ያለ ምግብ፣ መፀዳጃ ቤት ሳንሄድ እንድንሰራ እየተገደድን ነዉ” ብለዋል።

አክለውም “አሁን ላይ ለስራ  በማይመች ሁኔታ፣ የምንሰራበት የማበረታቻ አበል ተቆርጦ እንድንሰራ እየተገደድን እንገኛለን፣ ምክንያቱ በዉል የማይታወቅ እና የትኛዉም የአስተዳደር ክፍል መጥቶ ስለጉዳዩ ሳያስረዳን በተደጋጋሚ የስራ ሰዓት ድልደላዉን ወደቀድሞዉ እንዲመለስ በአለቃዎቻችን ቅሬታችንን ለማድረስ ብንሞክርም ማንም የሚመለከተዉ አካል ሰብስቦ ለማውራት ፈቃደኛ አይደለም። ከግንቦት 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል የተባለዉ የስራ ሰዓት ፕሮግራም ዳግም ታይቶ ከሆስፒታሉ አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጠን እና ቀድሞ የነበረንን የስራ መነሳሳት በዚህ ምክንያት እንዳይበደል የሚመለከተዉ የመንግስት አካል በጉዳዪ ላይ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን ስንል በትህትና እንጠይቃለን” ብለዋል።

በዚህ ቅሬታ ዙርያ ለኢትዮጵያ ቼክ መልስ የሰጡት የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ያሬድ አግደው ናቸው። እርሳቸው ያደረሱን መልስ እንዲህ ይቀርባል:

“በመሠረቱ በአሁኑ ሰዓት ምንም የተወሰነ አስተዳደራዊ ውሳኔ የለም። ነገር ግን:

1. በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ-19 ታማሚዎች በተለይ የፅኑ ህሙማን ቁጥር በመጨመሩ አገልግሎቱን ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፣

2. እስከዛሬ ሰራተኛው ያለ በቂ እረፍት በየቀኑ በመስራት ላይ በመሆኑ የታዩ የአገልግሎት ጥራት ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆኑ እያንዳንዱ ባለሙያ በሳምንት ቢያንስ አንድ ቀን እንዲያርፍ የስራ ሰዓት ማስተካከያ ለማድረግ ታቅዷል፣

ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት የሰራተኞችን መብት እና ግዴታ ባገናዘበ መልኩ እንዲሁም ከተለያዩ ሆስፒታሎች በተወሰደው ልምድ መሠረት በአሁኑ ሰዓት እያንዳንዱ ሰራተኛ ከሀላፊዎቹ ጋር የተሻለ አሰራር ለመዘርጋት በመወያየት ላይ ይገኛል።

በተረፈ ገና ምንም አይነት ውሳኔ ባልተላለፈበት እና ቅሬታዎች ወደ የትኛውም የአስተዳደር ሀላፊዎች ባልቀረበበት ሁኔታ ቀድሞ ወደ ሚዲያ ማውጣት አላስፈላጊ ነው። ከውሳኔው በኋላ ጥያቄ ወይም ቅሬታ ያለው ግለሰብ በፅሁፍም ይሁን በአካል የሚመለከተውን የሆስፒታል ሀላፊ ቀርቦ መጠየቅ ይችላል። በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ባለሞያው በትጋት ከአስተዳደሩ ጋር በመናበብ ማህበረሰቡን እያገለገለ የሚገኝ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል።”

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::