የአሜሪካ ሴኔት ‘S3199’ የተባለውን ህግ አፀደቀ በሚል ሰሞኑን የተሰራጩት መረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው። ታድያ እውነታው ምንድን ነው?

የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ‘S3199’ በሚል የኮድ ስያሜ የሚታወቀውንና “በኢትዮጵያ ሠላምና ዴሞክራሲን ለማበረታታት” (The Ethiopia Peace and Democracy Promotion Act) የሚል ርዕስ ያለውን ረቂቅ ህግ አጸደቀ የሚሉ መረጃዎች በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ሲሰራጭ ተመልክተናል።

መረጃውን ካሰራጩት መካከል ከ28,700 በላይ ተከታዮች ያሉት ‘Link Wolayta’ የተባለ የፌስቡክ ገጽ፣ ከ43,700 በላይ ተከታዮች ያሉት ‘Tigrai Online’ የተባለ የትዊተር አካውንት እና ከ2,200 በላይ ተከታዮች ያሉት ‘AwassaGuardian’ የተባለ የትዊተር አካውንት ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት S3199 የሚል የኮድ ስያሜ ያለውን ረቂቅ ህግ አጸደቀ የሚለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን አረጋግጧል።

በአሜሪካ ምክር ቤቶች ህግ የማውጣት ስነ-ስርዐት መሰረት አንድ ረቂቅ ሰነድ “ህግ” ሆኖ ከመጽደቁና ተግባር ላይ ከመዋሉ በፊት በርካታ ሂደቶችን ያልፋል። ከላይ የተጠቀሰው ረቂቅ ህግም ይህን ሂደት የሚከተል ሲሆን በትናትናው ዕለት ለአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ቀርቦ ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ ወደሚቀጥለው ደረጃ አልፏል።

በአሜሪካ ምክር ቤቶች የሚታዩ የህግ ረቂቆች ሂደቶችን የሚከታተለው govtrack.us መረጃ ረቂቅ ህጉ ከውጭ ግንኙነት ኮሚቴው ካለፈ በኃላ ወደ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት ይቀርባል ይላል። የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ በረቂቅ ህጉ ላይ ተወያይቶ የሚያጸድቀው ከሆነ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይመራል። ቀጥሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ ህጉን የሚያጸድቀው ከሆነ ህግ ሆኖ ለመውጣት የአሜሪካ ፕሬዝደንት መፈረም አለባቸው።

ከላይ በተዘረዘሩት ጥቅል የህግ ማጽደቅ ሂደቶች መሃል ሌሎች ንዑሳን ሂደቶችና ምልልሶችም እንደሚኖሩ የአሜሪካ ምክር ቤቶች አሰራር ያሳያል።

በአሜሪካ ምክር ቤቶች የሚታዩ የህግ ረቂቆችን የመጽደቅ ዕድል የሚተነብየው Skopos Labs Inc. የተባለ ተቋም የS3199 የመጽደቅ ዕድል 4% መሆኑን በድረ-ገጹ አስነብቧል።

ይህን ረቂቅ ህግ ባለፈው ህዳር ወር ለምክር ቤቱ ያስተዋወቁት የኒው ጀርሲው ሴናተር ሮበርት ሜንዴዝ ሲሆኑ ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሰብዐዊ መብት ጥሰት በፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል። ረቂቅ ህጉ ጦርነቱ በሰላም እንዲቋጭ የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ፣ ከጦርነቱ ለማትረፍ በሚሰሩ እና ጦርነቱ እንዲባባስ ድጋፍ የሚያደርጉና የሚሳተፉ አካላት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል መሆኑም ይነበባል።

የኢትዮጵያ መንግስት ረቂቅ ህጉን እንደሚቃወም በተደጋጋሚ አሳውቋል። ለምሳሌ ብልፅግና ፓርቲ ከትናንት በስቲያ በፌስቡክ ገፁ እንዳስነበባው “ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 በመባል የሚጠሩት ረቂቆች በሰሜኑ ጦርነት ትክክለኛ አጥፊው ማን እንደሆነ በሚዛናዊነት ያላየ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል የደረሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እውቅና የማይሰጥ ይልቁንም አንድን ወገን ለመደገፍና እና ለመሸፈን የተረቀቀ ለመሆኑ አመላካች ነው” ብሏል።

በተመሳሳይም ‘HR6600’ የተባለ ረቂቅ ህግ ለአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን ምክር ቤቱ የካቲት 01/2014 ዓ.ም ረቂቅ ህጉን ለምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች፣ ፍትሕ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለጦር ኃይል አገልግሎቶች መርቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::