ለንግስት ኤልሳቤት የቀብር ስነ-ስርዐት ለንደን ከሄዱት ውስጥ በአውቶቡስ የተሳፈሩት አፍሪካውያን መሪዎች ብቻ አልነበሩም

መስከረም 12፣ 2015

በዛሬው የ “ማብራርያ” አምዳችን የአፍሪካ መሪዎች በአውቶብስ ተሳፍረው ስለሚያሳየው አነጋጋሪ ፎቶ እና ተዛማጅ መረጃዎች እናቀርብላችኋለን።

የንግስት ኤልሳቤት የቀብር ስነ-ስርዐት በለንደን ከተማ ሰኞ እለት ከመከናወኑ ከአንድ ቀን በፊት (እሁድ እለት) አዲሱን ንጉስ ለመተዋወቅ አንድ ፕሮግራም በበኪንግሀም ፓላስ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ወቅት አንድ ፎቶ በኬንያው አዲስ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ የማህበራዊ ሚድያ ገፅ ተለቅቆ ነበር። ፎቶውም ራሳቸው ሩቶ፣ የታንዛንያ ፕሬዝደንት እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በአውቶቡስ ተሳፍረው ያሳያል።

ይህንን ተከትሎ በርካታ መላምቶች፣ አስተያየቶች፣ ሴራ ትንተናዎች እንዲሁም ትችቶች ሲሰነዘሩ ተስተውለዋል።

በርካቶች የአፍሪካ መሪዎች በአውቶቡስ እንዲሳፈሩ መደረጉን እንደ ንቀት የቆጠሩት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ምዕራባውያን ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው ብለውታል።

“በእለቱ በአውቶቡስ ተሳፍረው የነበሩት የአፍሪካ መሪዎች ለብቻቸው ተለይተው ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ ቼክ ደርሰዋል። እኛም በዚህ ዙርያ ማጣራት አድርገናል።

በዚህም መሰረት በእለቱ በአውቶቡስ ተሳፍረው የነበሩት የአፍሪካ መሪዎች ብቻ እንዳልነበሩ ለመረዳት ችለናል። ክስተቱን ከስፍራው ሆነው የቀረፁ ጋዜጠኞች እንዲሁም በርካታ ሚድያዎች በዚህ ዙርያ መረጃ አጋርተዋል።

በእለቱ ከኬንያ እና ታንዛንያ ፕሬዝደንቶች በተጨማሪ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የዮርዳኖስ ንጉስ አብደላ፣ የኒውዚላንድ ጠ/ሚር ጃሲንዳ አርደርን፣ የካናዳ ጠ/ሚር ጀስቲን ትሩዶ፣ የብራዚል ፕሬዝደንት ጃይር ቦልሶናሮ፣ የሲንጋፖር ፕሬዝደንት ሀሊማህ ያኮብ፣ የኖርዌይ ንጉስ እና ንግስት፣ የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ዋልተር-ስቴንሜይር፣ የጣልያን ፕሬዝደንት ሰርጂዎ ማቴሬላ፣ የፖላንድ ፕሬዝደንት አንድሬይ ዱዳ፣ የአውስትራሊያ ጠ/ሚር አንቶኒ አልባኒዝ እንዲሁም የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን በአውቶቡስ ጉዞ እንዳደረጉ ታውቋል።

ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የራሳቸውን “ዘ ቢስት” ተብሎ የሚጠራውን ብረት ለበስ መኪና ተጠቅመው ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ተዘግቧል።

ይህ ለምን እንደሆነ ዘ ኢንዲፔንደንት ሲያብራራ “ለፕሮግራሙ ፀጥታ እና ለሁሉም ደህንነት ሲባል የክቡር እንግዶች መኪናቸውን እና ጠባቂዎቻቸውን Royal Hospital Chelsea የሚባለው ስፍራ እንዲያቆሙ ተደርጓል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ካለባቸው ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የተነሳ በራሳቸው መኪና እንዲጓዙ ተደርጓል” ብሏል።

በዚህ ዙርያ በተለይ በርካታ አፍሪካውያን ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም የኒውዝላንድ ጠ/ሚር ጃሲንዳ አርደርን ለቢቢሲ “ይህ ምንም ማለት አይደለም… ለደህንነት ሲባል ነው። ከዚህ ቀደምም ለኮመንዌልዝ ስብሰባ ስንመጣ አውቶቡስ ተጠቅመናል፣ ይሄ ያለ ነገር ነው” ብለዋል።

ስለዚህ በበርካታ ሚድያዎች እና ማህበራዊ ሚድያ ገፆች የአፍሪካ መሪዎች ለብቻቸው ተለይተው በአውቶቡስ እንዲጓዙ መደረጋቸው የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ማየት እንችላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::