የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አሳሳቢነት በስፋት የተነገረበት የፕረስ ነፃነት ቀን አከባበር በኢትዮጵያ!

የአለም የፕረስ ነፃነት ቀን በትናንትናው እለት ለ30ኛ ግዜ በአለም ዙርያ ተከብሮ ውሏል። በኢትዮጵያ ደግሞ እለቱ በዛሬው እለት በስካይላይት ሆቴል “መረጃ ለህዝብ ጥቅም” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።

በዚህ ወቅት ተደጋግሞ የተነሳው ጉዳይ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አሳሳቢነት ነው። የስርጭቱ መጠን እየሰፋ ስለመጣ ሚድያዎች፣ የመረጃ አጣሪ ተቋማት፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ የውጭ ተቋማት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ተብሏል።

“የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ሀገራችንን ለአደጋ አጋልጧታል” ያሉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ “ይህ የመረጃ መዛባት በፕረስ ነፃነት ላይም አደጋ ደቅኗል” ብለዋል።

በፕሮግራሙ መሰረት በሀሰተኛ መረጃ ዙርያ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያ ቼክም ሀሳብ እንዲያቀርብ ተጋብዟል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::