ስለ አሳሳቢው እና አዲሱ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን ማወቅ ያለብን ነጥቦች!

አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ልውጥ ዝርያ (ኦሚክሮን) ትልቅ ስጋት መደቀኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ አስታውቋል። የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው አዲሱ ልውጥ ዝርያ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው በራሄያዊ ለውጥ (mutations) ያደረገ ሲሆን ይህም ክትባቶችን የመቋቋምና በፍጥነት የመዛመት ዕድል ይሰጠዋል የሚል ሰጋትን ፈጥሯል።

አዲሱን ልውጥ የኮሮና ቫይረስ መለየት የቻሉት የደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ የተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ሲሆኑ የዓለም የጤና ድርጅት በጣም አሳሳቢ ከተባሉ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች (Variant of Concern) መዝገብ ውስጥ አስፍሮታል።

ስለ አዲሱ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ምን ይታወቃል?

በአሁኑ ሰዐት የደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ የተለያዩ ሀገሮች ተመራማሪዎች ኦሚክሮን የተሰኘ መጠሪያ የተሰጠውን ይህን አዲስ ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የበለጠ ለመረዳት ምርምር በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በደቡባዊ የአፍሪቃ ክፍለ አህጉር በአዲሱ ልውጥ ዝርያ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ቢሆንም ቀደም ካሉት የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች አንጻር የኦሚክሮን ከሰዎች ወደ ሰዎች የመዛመት ፍጥነቱን በአሁኑ ሰዐት ይህ ነው ለማለት አዳጋች መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዝርያውን አስመልክቶ ወቅታዊ መረጃ በሚያጋራበት የድረ-ገጽ ክፍሉ አስነብቧል።

በደቡብ አፍሪቃ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል ለመተኛት የሚገደዱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን የገለጸው ድርጅቱ ነገር ግን የበሽታውን ጽኑነት ለመረዳትም ሆነ ቀደም ካሉት ዝርያዎች የተለየ የህመም ምልክት ስለማስከተሉ ለማወቅ ጊዜ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል። በሽታው በመጀመሪያ ወጣት በሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ መታየቱንም አስታውሷል።

አዲሱ ልውጥ ዝርያ ለክትባቶች የሚሰጠውን ምላሽ ለመረዳትም ምርምር እየተደረገ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ጨምሮ አስታውቋል። ሆኖም የኮቪድ-19 ወረርሽን መከላከያ ክትባቶች ከጽኑ ህመምንና ከሞትን እንደሚታደጉ አስምሮበታል።

አዲሱን ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መገኘት ተከትሎ በርከት ያሉ ሀገሮች ለደቡብ አፍሪቃና ለጎረቤቶቿ በራቸውን ዝግ ያደረጉ ሲሆን ይህም በዓለም የጤና ድርጅት ተኮንኗል። አዲሱ ልውጥ ዝርያ ከደቡብ አፍሪቃ በተጨማሪ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በቤልጅየም፣ በፖርቹጋል፣ በሆንግኮንግ፣ በጣሊያን፣ በጀርመን እና በሌሎች ሀገሮች ተከስቷል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚንስር ዶክተር ሊያ ታደሰ በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው አዲሱን ልውጥ ዝርያ በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሁፍ ህብረተሰቡ የመከላከያ ክትባት እንዲወስድ አሳስበዋል። ሚንስትሯ “የኮቪድ 19 ክትባት፣ በቫይረሱ የመያዝን፣ ከተያዙም በጠና መታመምን እንዲሁም በበሽታው የመሞትን እድል በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንሰው በመረጋገጡ ለጤናችን እና ለህይወታችን ብለን በስፋት እየተሰጠ ያለውን ክትባት ዛሬ ነገ ሳንል እንከተብ!” ብለዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::