የፌስቡክ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን በተለከተ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር በትናንትናው ዕለት ባወጣው ረዘም ያለ መግለጫ አስታውቋል። 

ኢትዮጵያን ከሁለት ዓመት በፊት “ለግጭትና ለአመጻ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው” ካላቸው ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ማስገባቱን የገለጸው ሜታ በዚህም እፎይታ ሰጭ መፍትሄዎችንና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅዎችን መቅረጹን አትቷል። የትኩረት አቅጣጫዎቹም ፖሊሲዎቹን የሚጥሱ መልዕክቶችን ማስወገድ፣ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ማክበርና ሰዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መርዳት መሆኑን ገልጿል። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት ሪፖርት የማድረጊያና የማስፈጸሚያ መገልገያዎቹን ማዘመኑን ያስታወቀው ሜታ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በስፋት በሚነገሩ አራት ቋንቋዎች (አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ሱማሌኛና ትግርኛ) የሚጋሩ መልዕክቶችን መገምገም መቻሉን ገልጿል። በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ የሚተላለፉ የጥላቻ መልዕክቶችን ሪፖርት ከመደረጋቸው በፊት መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ማበልጸጉን አመልክቷል። 

በዚህም እ.አ.አ ከግንቦት እስከ ጥቅምት 2021 ዓ.ም ከ92 ሺህ በላይ የጥላቻ ንግግር ደንቦችን ጥሰዋል ያላቸውን የፌስቡክና የኢንስታግራም ይዘቶች ማስወገዱንና ከነዚህም መካከል 98 በመቶዎቹ ሪፖርት ከመደረጋቸው በፊት የተለዩ መሆኑን አስታውቋል። በተጨማሪም በሰኔ ወር 2021 ዓ.ም በተቀናጀ መልክ የተቃዋሚ ፖለቲከኞ/ቡድኖች ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበር ያላቸውን ሀሠተኛ አካውንቶችን ማገዱን የገለጸ ሲሆን በመጋቢት ወር 2021 ዓ.ም መቀመጫቸውን ግብጽ በማድረግ ኢትዮጵያን፣ ሱዳንንና ቱርክን ኢላማ አድርገው ነበር ያላቸውን አካውንቶች መዝጋቱን አስታውሷል። 

አሁን በሀገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተገናኘ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰዱንም ሜታ በመግለጫው አስነብቧል። ከእርምጃዎቹ መካከል ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶች ተደራሽነታቸው እንዲቀንስ ማድረግ፣ ግጭትን የሚያነሳሱ መልዕክቶችን እንዲሁም በቡድኖች ላይ ብቀላንና ጥቃትን የሚገፋፉ መግለጫዎችን ማስወገድ የሚሉ ይገኙበታል። 

እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑ ነውጠኛ ቡድኖች (Violent Non-State Actors) ላይ የሚወስደውን እገዳ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትና አባቶርቤ የሚባሉ ቡድኖች ላይ የወሰደውን የእግድ እምጃ ጠቅሷል። የጥላቻ ንግግር ደንቦቹንም አጠናክሮ እንደሚቀቀጥል የገለጸው ሜታ በኢትዮጵያ በስፋት በሚነገሩ አራት ቋንቋዎች የጥላቻ ይዘት ያላቸውን በርካታ ቃላቶች መለየቱንም አስታውቋል። አዳዲስ የጥላቻ ቃላት የመለየት ስራ እንደሚከውንም ገልጿል። ሜታ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን እንዲሁም ለጥቃት የሚያነሳሱ ይዘቶችን የማስወገድ ስራውን በበለጠ ትኩረት እንደሚሰራም አስታውቋል። 

በተጨማሪም ለኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎቹ ሎክ ፕሮፋይል (Lock Profile) የተባለ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህም ተገልጋዮች ጓደኛቸው ያልሆነ ሰው የፕሮፋይል ፎቷቸውን እንዳያወርድ፣ ጎላ አድርጎ እንዳይመለከትና እንዳያጋራ ያስችላል። እንዲሁም ጓደኛ ያልሆነ ተጠቃሚ አዲስም ሆኑ የቆዩ መልዕክቶችንና ፎቶዎችን እንዳያይ፤ የጓደኛ ዝርዝር እንዳይመለከት ያደርጋል። 

ሜታ ለዚህ ተግባሩ የተቀናጀ የኦፕሬሽን ማዕከሉን (Integrated operation Center) ማንቀሳቀስ መጀመሩንና ያሉትን ባለሙያዎች ማሰማራቱን ገልጿል። 

ሜታ በኢትዮጵያ ፕላትፎርሞቹን በመጠቀም ለሚሰራጩ የጥላቻ፣ ግጭት ቀስቃሽና ሀሠተኛ መረጃዎች ትኩረት አልሰጠም ተብሎ በተለያዩ ወገኖች የሚወቀስ ሲሆን በቅርቡ የድርጅቱ የቀድሞው ሰራተኛ ፍራንሲስ ሀውገን ለአሜሪካ ኮንግረስ ምስክርነቷን መስጠቷ ይታወሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::