“እንዴት በዳግማዊ ሚኒሊክ ስም የሚጠራ ሆስፒታል ስሙን ይፍቃል? ስሙ መሬት ላይ በመሆኑና በተላላፊ ሰዎች ስለሚረገጥ ግድግዳ ላይ ለመለጠፍ እየተሰራ ነው”— የሚኒሊክ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ሐብተዮሃንስ ለኢትዮጵያ ቼክ 

ባለፉት ጥቂት ቀናት በዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተነሳና “MINILIK” የሚል በእንግሊዘኛ የተጻፈን ጽሁፍ መዶሻና መሮ የያዘ ሰው ሲቆረቁር የሚያሳይ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲዘዋወር ተመልክተናል። 

ከፎቶው ጋር ‘’ሚኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ በሴራሚክ  ‘MINILIK’ ተብሎ ታትሞ የነበረውን ቅርጽ እያጠፉት ነው’’ የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች አብረው ሲጋሩ እንደነበርም አስተውለናል። 

በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታዮችም “ምን እየተከናወን እንደሆነ አጣሩልን” የሚሉ መልዕክቶችን አድርሰውናል።  

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ ከሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ሐብተዮሃንስ ማብራሪ ጠየቋል። ዶክተር ታደሰ በሴራሚክ የተጻፈውን ጽሁፍ እያጠፉት ነው የሚለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የገለጹ ሲሆን “እንዴት በዳግማዊ ሚኒሊክ ስም የሚጠራ ሆስፒታል ስሙን ይፍቃል?” ሲሉ ጥያቄ አዘል መልስ ሰጥተዋል። 

ዋና ስራ አስኪያጁ በፎቶው ላይ የሚታየው በህንጻ ግንባታ ወቅት በግንባታ ግብዓቶች መፋፋቅና ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የስሙ ክፍል ማስተካከያ ሲደረግለት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል። ዶክተር ታደሰ ስሙ መሬት ላይ በመሆኑና በተላላፊ ሰዎች ስለሚረገጥ በተሻለ ግብዐት የተሰራ ጽሁፍ በማሰራት ግድግዳ ላይ ለመለጠፍ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፣ ይህም በቅርቡ እንደሚሆን ለኢትዮጵያ ቼክ አብራርተዋል። 

ዋና ስራ አስኪያጁ “ፎቶውን ያነሳው ሰው መልካም ነገር ቢያስብ ከተሻለ አንግል መውሰድ ይችል ነበር” በማለት ቅሬታ አዘል አስተያየትም ሰጥተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::