ተመሳሳይ አርዕስት፣ ይዘት እና ቅርፅ ያለው ዜና ይዘው እየወጡ የሚገኙ ሚድያዎች!

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገራችን ያሉ ትልልቅ የሚባሉ ሚድያዎች በምስሉ ላይ በሚታየው መልኩ ተመሳሳይ አርዕስት፣ ይዘት እና ቅርፅ ያላቸው ዜናዎችን በብዛት ይዘው ሲወጡ ይታያል። እነዚህ ሚድያዎች ዜናዎቻቸውን ሚያቀርቡትም በደቂቃዎች ልዩነት ሲሆን ይህም በርካቶች ላይ ግርምትን ፈጥሯል፣ እየፈጠረም ይገኛል።

እንዲህ አይነት አሰራር በርካታ ጉድለቶችን እንደሚያመጣ፣ እንዲሁም ስህተት ሲከሰት ተያይዞ መጥፋትን ሊያስከትል እንደሚችል መገመት ይቻላል።

በመጀመርያ ሊያመጣ የሚችለው ጉድለትን እንመልከት:-
እነዚህ በመንግስት/በህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱ ሚድያዎች በርካታ ልምድ፣ ሀብት እና እውቀት ያዳበሩ ናቸው። የሚያቀርቧቸው ዘገባዎችን ህዝብን ሊያሳውቁ የሚችሉ፣ ችግሮችን ነቅሰው አውጥተው ለመፍትሄ የሚያመቻችቹ እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትብብርን የሚያመጡ ሊሆኑ ይገባል። ከዛ በተቃራኒ ከሌሎች ሚድያዎች ኮፒ/ፔስት በማድረግ ገፆቻቸውን ማጨናነቃቸው እንደሀገር የሀብት እና የእውቀት ጉድለትን ያስከትላል።

በዘገባዎች ላይ ስህተት ሲከሰት የሚኖረውን አንድምታ እንመልከት:-
በቅርቡ በበርካታ የመንግስት፣ የግልም ይሁን የአለም አቀፍ ሚድያዎች ላይ በብዛት እንደተስተዋለው ሀሰተኛ መረጃዎችን የያዙ በርካታ ዘገባዎች ሲወጡ ተስተውሏል። ከላይ የጠቀስነው አይነት የኮፒ/ፔስት አሰራር ሀሰተኛ መረጃዎች ሲከሰቱ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰራጩ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ሚድያዎች ዜናዎችን ከሰበሰቡ በሗላ ካለ ምንም ለውጥ ከማቅረብ ይልቅ የራሳቸውን የዜና እይታ (angle) በመምረጥ ትንታኔዎችን መስጠት፣ የራስ (exclusive) ቃለ-መጠይቆችን በማድረግ ዘገባውን ማዳበር እንዲሁም የዜናውን ይዘት ቀያይሮ በማቅረብ ተደራሲያን የተለያየ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል።

በዚህ ረገድ የሀገር ውስጥ ሚድያዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ስራ ሲሰሩ ይታያል፣ ዜናዎችን አከታትለው የሚያቀርቡ ትልልቅ ሚድያዎች ከእነዚህ የሀገር ውስጥ ሚድያዎች ብዙ ሊማሩ ይገባል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::