ከአመታት በፊት ተዘግቶ የነበረው የአህያ ቄራ አሁን ስራ ጀመረ በመባሉ ዙርያ ሚድያዎች ያወጧቸው መረጃዎች!

ባለፉት ጥቂት ቀናት በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በአሰላ ከተማ ከሰባት ዓመት በፊት ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባው እና ከማኅበረሰቡ በተነሳ ተቃውሞ ሳቢያ ሥራውን አቁሞ የነበረው የአህያ ቄራ እንደገና ስራ ጀመረ መባሉ ዋነኛው ነው። ጉዳዩን በተመለከተም ሳምንታዊው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ አዲስ ፎርቹን፣ ቢቢሲ አማርኛ እንዲሁም ሸገር ሬዲዮ ዘገባዎችን ሰርተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ በርካታ ጥያቄዎች የደረሱት ሲሆን የሚድያ ቅኝት በማድረግ ይህንን መረጃ አሰባስቧል።

አዲስ ፎርቹን ሆንግ ቻንግ በተባለ የቻይና ኩባንያ የሚተዳደረው የአሰላ የአህያ ቄራ ስራ መጀመሩን የዘገበ ሲሆን ባለፈው ወር 80 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ስጋ ወደ ምስራቅ እስያ ገበያ ማቅረቡን አስነብቧል። ስጋውን ለማጓጓዝ የሚያግዙ ማቀዝቀዣ ኮንቴነሮችን የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማቅረቡንም አዲስ ፎርቹን ዘግቧል።

ጋዜጣው ያነጋገራቸው በአሰላ ከተማ የሂላል ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ቃሲም ኢብራሂም ከአካባቢው የሀይማኖት አባቶች፣ ከማህበረሰብ መሪዎች እንዲሁም ከአሰላ ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናትና የጸጥታ ኣአካላት ጋር ከተደረገ ምክክር በሗላ ቄራው ስራ መጀመሩን ገልጸዋል። በተደረገው ምክክርም ቄራው ከአካባቢው ለእርድ የሚሆኑ አህዮችን አይገዛም ብለዋል።

በሌላ በኩል ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአሰላ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ቀመሪያ ሳኖ “ፋብሪካው ወደ ሥራ እንዳልተመለሰ ነው የምናውቀው’’ ሲሉ ገልጸዋል። ፋብሪካው ከሰባት ዓመት በፊት መዘጋቱን የሚገልጹት ኃላፊዋ “እኛም ብንሆን እስካሁን እንደተዘጋ ነው የምናውቀው፤ ለፋብሪካው ፈቃድ የተሰጠው በፌደራል መንግሥት ነው፤ አሁንም ቢሆን ፈቃዱ ይቀጥል ወይስ አይቀጥልም የሚለውን የሚወስኑት እነርሱ ናቸው’’ በማለት ተናግረዋል።

ነገር ግን ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአህዮች ደኅንነት ላይ የሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት፣ ዶንኪ ሳንክችዋሪ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጂአ ሂንደቡ ፋብሪካው እንደገና ስራ መጀመሩን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረጃ እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል። ይህንኑ በተመለከተም ጉዳዩ ለሚመለከተው የግብርና ሚኒስቴር አቅርበው “ፋብሪካው አልተከፈተም” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ሸገር ሬዲዮ በበኩሉ ቄራው በድብቅ ስራውን እንደገና ጀምሯል ሲል ዘገባ ሰርቷል። በሸገር ዘገባ መሰረት ቄራው ‘Manufacturing PLC’ የሚል ስያሜ የሚጠቀም ሲሆን እርዱን የሚያከናውነውም ማታ ማታ ነው። ሸገር ያነጋገራቸው የጋማ እንስሳት ላይ የሚሰራው ብሩክ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳሬክተር አቶ ደስታ አረጋ ቄራው እንደገና ስራ መጀመሩን በአካል ተገኝተን አረጋግጠናል ብለዋል።

ለሙሉ ዘገባዎቹ እነዚህን ሊንኮች ይከተሉ:

አዲስ ፎርቹን: https://addisfortune.news/donkey-slaughterhouse-opens-after-seven-year-deadlock/?fbclid=IwAR1IhLFDqH7SsMYTb21lmuORtL8btBaie0_yD2flVxzREUugcR2j6a28_VU

ቢቢሲ አማርኛ: https://www.bbc.com/amharic/news-58858216?at_custom4=D5E3A8FA-2B2A-11EC-BBE7-62F0923C408C&at_custom2=facebook_page&at_custom1=%5Bpost+type%5D&at_custom3=BBC+News+Amharic&at_campaign=64&at_medium=custom7&fbclid=IwAR3U9CZiAApCbb8PS2rp0nWVyx0RwgIWTgk0ylyb1CY1CHhHsnzkxQjGQA8

ሸገር ኤፍኤም: https://www.mixcloud.com/ShegerFM/%E1%8C%A5%E1%89%85%E1%88%9D%E1%89%B5-4-2014-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%8B%8D-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%85%E1%8B%AB-%E1%89%84%E1%88%AB-%E1%89%A0%E1%8B%B5%E1%89%A5%E1%89%85-%E1%88%A5%E1%88%AB-%E1%8C%80%E1%88%9D%E1%88%AB%E1%88%8D/?fbclid=IwAR31tLpRVq50bT8NZ23176yzqvNbpqoKXKnPatuT-QR7jRQ1vGQu0BraV6Q

Photo: social media

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::