“የቦረና ብሔራዊ ፓርክ” ወይስ “ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ”?

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በትናትናው ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ቦረና ብሔራዊ ፓርክ የሚል ጽሁፍ የሜዳ አህዮች ከሚታዩባቸው ፎቶዎች ጋር ለጥፈዋል። 

ይህን ተከትሎ በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አቶ አዲሱ በደቡብ ክልል የሚገኘውን ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ “ቦረና ብሔራዊ ፓርክ አሉት” የሚሉ ቅሬታዎችን ሲያቀርቡ ተመልክተናል። አማን ሻሎም የተባለና ከ7,000 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ ቦረና ብሔራዊ ፓርክ የሚባል የህግ ዕውቅና ያለው ፓርክ ስለመኖሩ ጥርጣሬውን የገለጸ ሲሆን በፎቶግራፎቹ የሚታዩት የሜዳ አህያ ዝርያዎችም በተጠቀሰው ፓርክ ስለመኖራቸው ጥያቄ አንስቷል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን ለማጣራት አቶ አዲሱን እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለስልጣንን አነጋግሯል። በተጨማሪም ሰነዶችንና ካርታዎችን ተመልክቷል። 

አቶ አዲሱ ፎቶግራፎቹን የተነሱት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ደቡባዊ ክፍል መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ የተናገሩ ሲሆን ነጭ ፓርክ ነው ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሀሠት መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ቦረና የሚባል ብሔራዊ ፓርክ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁን የጠየቀ ሲሆን “አዎ አለ” የሚል ምላሽ አግኝቷል። አቶ ሰለሞን ቦታው ቀደም ሲል የያቤሎ እንስሳሳት መጠበቂያ (Yabello Wildlife Sanctuary) በሚል ስያሜ ይታወቅ እንደነበር ገልጸው በክልሉ መንግስት ጥያቄ ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ማደጉን አስረድተዋል። በፓርኩ ውስጥም መደበኛ የሜዳ አህዮች እና ትልቁ የሜዳ አህያ (Gravy’s Zebra) እንደሚገኙ አረጋግጠዋል። 

የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በ573 ኪሎሜትሮች እርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በ200 ኪሎሜትሮች ይርቃል። 2,500 ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍነው ይህ ፓርክ በውስጡ በርካታ አጥቢ እንስሳሳት እና አዕዋፋት ይኖሩበታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::