በአፄ ሀይለስላሴ ዘመን በነበረው የኢትዮጵያ ሀምሳ ብር ኖት ላይ የሚታየው ምስል የህዳሴ ግድብ ፕላን ወይስ ሌላ?

– በአፄው ዘመን በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት የነበሩ እቅዶችስ ነበሩ?

የዛሬ ወር ገደማ የህዳሴ ግድብ ሀይል ማመንጨት መጀመሩን ተከትሎ በርካታ ፅሁፎች እና መላ ምቶች ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲንሸራሸሩ ነበር።

ከነዚህም መሀል ከታች በምስሉ ላይ የሚታየው የቀድሞው የኢትዮጵያ ሀምሳ ብር ኖት ላይ የተቀመጠው የግድብ ምስል የህዳሴ ግድብን ንድፍ ወይም ፕላን ያሳያል የሚል ይገኝበታል። በነዚህ ፅሁፎች የተቀመጡት መላ ምቶች እንደሚሉት አባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት እቅድ ተሰርቶ የነበረው በቅርብ አመታት ሳይሆን በአፄ ሀይለስላሴ ዘመን ነበር።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ታሪካዊ መፃህፍትን እና የተለያዩ መረጃዎችን በመዳሰስ የሚከተለውን መረጃ አሰናድቷል።

– በቀድሞው የሀምሳ ብር ኖት ላይ የሚታየው የግድብ ምስል የህዳሴ ግድብን ንድፍ ያሳያል?

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ በርካታ መረጃዎችን የተመለከተ ሲሆን ምስሉ የቆቃ ግድብን እንጂ የህዳሴ ግድብን ንድፍ እንደማያሳይ አረጋግጧል።

ለምሳሌ ይህ ካርድካው የተባለ የፖስትካርድ አምራች ድርጅት የቆቃ ግድብ ምስል ያለበትን ስራውን በወቅቱ ከምስሉ ጋር ለሽያጭ አቅርቦ ነበር (https://www.cardcow.com/816467/ethiopia-koka-dam-lake-gelila-africa/)።

ከዚህ በተጨማሪም የባንክ ኖቶች ሙዚየም የሚታየው ምስል የቆቃ ግድብ እንደሆነ ይጠቁማል (http://www.banknote.ws/COLLECTION/countries/AFR/ETH/ETH0028.htm)።

በጉዳዩ ዙርያ ጥናት ያረጉት ፕሮፌሰር ጄይ ኔይሰን እንዳሉትም “በብር ኖቱ ላይ የሚታየው ምስል የቆቃ ግድብን ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተቀርፆ አየር ላይ የዋለ ይህ የቅርብ ግዜ የቆቃ ግድብ ቪድዮም የብር ኖቱ ላይ ከሚታየው ምስል ጋር ተመሳሳይ ነው (https://youtu.be/m5sEFZSwBp4)።

የቆቃ ግድብ የአዋሽ ተፋሰስ አካል ሲሆን ኤሌክትሪክ ከማመንጨትም በተጨማሪ ለቱሪስት መስህብነት እንዲሁም በዓመት ከ625 ቶን በላይ የዓሳ ምርት የሚገኝበት ነው፡፡

– በአፄው ዘመን በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት የነበሩ እቅዶች ነበሩ?

ታሪካዊ ፅሁፎች እንደሚጠቁሙት በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት መጀመሪያ ሊባል የሚችል ጥናት የተደረገው እ.አ.አ በ1935 በጣልያን ወረራ ወቅት ነበር። ይህ ባይሳካም ተከታታይ ጥረቶች መደረጋቸውን ቀጥለው ነበር።

ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ “Ethiopia and the Nile” በሚል እ.አ.አ በ 2007 ባሳተሙት መፅሀፍ ላይም ይህን አረጋግጠው “በአባይ ወንዝ ላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመስራት እቅዶች መያዝ የጀመሩት እ.አ.አ በ1930ቹ ነበር፣ ከነዚህም በጣና ሀይቅ ላይ ሊሰራ ታስቦ የመከነው እቅድ አንዱ ነው” ብለዋል።

አቶ ሀይሉ ወልደ ጊዮርጊስ “ለአባይ ውሀ ሙግት” በሚለው መፅሀፋቸው በ1950ዎቹ በአባይ ወንዝ ላይ የመስኖ እና የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን ለመስራት እቅድ እንደነበር ያስረዳሉ። “በወቅቱ ከአሜሪካን መንግስት ጋር ቅርበት ስለነበራት ትብብር ለማግኘት ብዙም ችግር አልገጠማትም። በዚሁ ምክንያት ከአሜሪካን የእርሻ መሬት ማልሚያ ቢሮ ጋር አንድ ውል ለመፈረም ችላለች። በአሜሪካኖች በወቅቱ የተካሄደው የአባይ ጥናት ዋናው ግብ የተፋሰሱን ሀብት (የኤሌክትሪክ ሀይልን ጨምሮ) ኤንቬንተሪ ለመያዝ ነበር። ይህን ተከትሎ ጥቅም ያስገኛሉ ተብለው የተገመቱት እቅዶችን ለይቶ የመዘርዘር እና ወጪውን የማስላት ስራ ተከናውኖ ነበር” ብለው አስፍረዋል።

እ.አ.አ በ1964 የወጣው “Land and water resources of the Blue Nile” የተባለ ጥናት እንዳመላከተው 8 ቢልዮን ተኩል ሜትር ኪዩብ ውሀ ሊይዙ የሚችሉ ግድቦችን ለመገንባት 71 አመቺ ስፍራዎች፣ 31 የዝናብ ውሀ ማጠራቀሚያዎች እንዲሁም 19 የሀይል ማመንጫ ጣብያዎች ተለይተው ታውቀው ነበር። በአሜሪካ በወቅቱ ከቀረቡ እቅዶች መሀል በጥቁር አባይ ወንዝ ላይ፣ በጣና ሀይቅ ላይ፣ በካራደቢ ማቢል እና በሱዳን ጠረፍ በሚንዳያ ላይ አራት ግድቦች እንዲገነቡ የሚል ነበር።

ከላይ የጠቀስነው የፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ መፅሀፍ ይህን ደግፎ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1958 (በአፄው ዘመን) የአባይ ተፋሰስ ልማት ፕላን ማውጣት ጀምራ ነበር። ለዚህም የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ ተጠይቆ የነበረ ሲሆን የአሜሪካው Bureau of Reclamation of the US Department of Interior ይህን ስራ እንዲሰራ ተመድቦ ነበር፣ ለዚህም ሁለቱ ሀገራት ለጥናት የሚያስፈልገውን ወጪ በጋራ ሊሸፍኑ ተስማምተው ነበር። ኢትዮጵያ ለጥናቱ 42 ሚልዮን ብር አውጥታ ነበር (በወቅቱ አንድ የአሜሪካ ዶላር ሁለት ብር ይመነዘር ነበር)።

ይህ ሁሉ ጥናት የአባይ ወንዝ ላይ ተካሂዶ የነበረ ቢሆንም የዛሬ አስር አመት የህዳሴ ግድብ (በወቅቱ የሚሊኒየም ግድብ ይባል ነበር) ግንባታው እስኪጀመር ተግባር ላይ አልዋለም ነበር።

ይህን ፕሮፌሰር ያቆብ ሲያስረዱ በ1959 በግብፅ እና ሱዳን መካከል የተፈረመው እና ለአስዋን ግድብ መገንባት ምክንያት የሆነው ክስተት አንዱ ነው ይላሉ። አክለውም የአስዋን ግድብ በሶቪየት ህብረት፣ የኢትዮጵያ የአባይ ግድብ ጥናት ደግሞ በአሜሪካ መከናወኑ ከቀዝቃዛው ጦርነት ሂደት ጋር እንደሚያያዝ አብራርተዋል።

ይህንን መረጃችንን አፄ ሀይለስላሴ እ.አ.አ በ1957 በዚህ የአባይ ጥናት መጀመር ዙርያ ባደረጉት ንግግር እንቋጭ:

“ኢትዮጵያ ይህን ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለመጋራት እና ችሮታውንም ለመካፈል ትፈልጋለች። ሀገራችን ያላትን የውሀ ሀብት ማልማት እና እያደገ ያለውን ኢኮኖሚዋን እና የህዝቧን ፍላጎት ማሟላት ሀላፊነቷ ነው። ይህን ለማሳካት በዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት አስጀምረናል።”

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::