ክትባቱ በመጀመርያ የሚሰጠው ለመንግስት ሀላፊዎች ነው?

“ክትባቱ በመጀመርያ የሚሰጠው ለመንግስት ሀላፊዎች ነው”— ካፒታል ጋዜጣ

“የጤና ባለሙያዎች እና እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ ግለሰቦች በቅድሚያ ክትባቱን ያገኛሉ”— የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለኢትዮጵያ ቼክ

የመጀመሪያዎቹ የኮቪድ-19 ክትባቶች በትናንትናው እለት ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደርሰዋል፣ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በኮቫክስ የግዢ ስርዓት የተገኙ የመጀመሪያዎቹን 2.2 ሚሊዮን ክትባቶች ትናንት ተረክባለች።

በርክክቡ ስነ ስርአት ወቅት እንደተገለፀው ክትባቶቹ በህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት የተመረቱ የአስትራ ዜኔካ ክትባቶች ናቸው። በርክክቡ ወቅት በይፋ እንደተገለፀው በርካታ ሀገራት እንደሚያደርጉት ክትባቱ በቅድሚያ የሚሰጣቸው ቫይረሱን በመዋጋት ረገድ ግንባር ቀደም ለሆኑት የጤና ባለሙያዎች እና እድሜያቸው ለገፉ ሰዎች ነው።

ይሁንና ካፒታል ጋዜጣ ትናንት በፌስቡክ ገፁ እና በድረ-ገፁ እንዳስነበበው ክትባቱ በመጀመርያ የሚሰጠው ለመንግስት ሀላፊዎች ነው ብሏል። ይህንን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ ከጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ መረጃ ጠይቋል።

ዶ/ር ሊያ ጋዜጣው መረጃውን ከየት እንዳገኘው እንደማያውቁ ገልፀው የጤና ባለሙያዎች እና እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ ግለሰቦች በቅድሚያ ክትባቱ እንደሚሰጣቸው አብራርተዋል።

አክለውም “ጥቂት የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የክትባቱ መጀመርን በማስመልከት እና ለሌሎችም አርአያ በመሆን ለማሳየት ሊከተቡ ይችላሉ” ብለው ለኢትዮጵያ ቼክ የገለፁ ሲሆን በአጠቃላይ ግን የመንግስት ሀላፊዎች የመጀመርያ ክትባት ያገኛሉ መባሉ ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::