በአንጻራዊነት ‘ታማኝ’ የሚባሉ ሚዲያዎችን በቀላሉ ለመለየት እና ለመከተል የሚረዱ እነዚህ ነጥቦችን ልብ ይበሉ!

በየዕለቱ የመረጃ ፍላጎታችንን ለማሟላት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ እንከፍታለን፤ ወደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩትዩብ ወይም ቴሌግራም አካውንታችን እናማትራለን። መረጃ የሚያቀርበው መደበኛም ሆነ መሰረቱን ዲጅታል ያደረግ ሚዲያ ብዙ ነው። ሁሉም ሚዲያዎች ግን ትክክለኛ መረጃ ይሰጡናል ማለት አይደለም፣ ይህም ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ሊያጋልጠን ይችላል።

ከታች የተዘረዘሩትን መስፈርቶች በጥንቃቄ መመልከት በአንጻራዊነት ታማኝ የሆኑ ሚዲያዎችን በቀላሉ ለመለየት ይረዱናል።

1. የጋዜጠኝነት ሙያን መሰረታውያንና የስነ-ምግባር መርሆችን ይተገበራሉ: በአንጻራዊነት ታማኝነት ያላቸው ሚዲያዎች የጋዜጠኝነት ሙያ መሰረታውያንና የስነ-ምግባር መርሆችን ይከተላሉ። ከሙያና ከስነምግባር መገለጫዎች መካከል ትክክለኛነት፣ ገለልተኝነት፣ ነጻነት፣ ፍትሐዊነት፣ አካታችነት ወዘተ ይጠቀሳሉ። ርዕሰ አንቀጾችን፣ የዜና ዘገባዎችን እና ሌሎች ይዘቶችን በጥንቃቄ ማስተዋል ሚዲያዎች ከላይ የተጠቀሱትን መገለጫዎች መተግበራቸውን ይነግሩናል። ለምሳሌ በዜና ዘገባ ላይ የተጠቀሰ ተቋም ወይንም ግለሰብ ሀሳቡ ተካቷል ወይም እንዲካተት ጥረት ስለመደረጉ ተጠቅሷል?

2. ግልጽነት ያሰፍናሉ: በአንጻራዊነት ታማኝነት ያላቸው ሚዲያዎች ስለራሳቸው በቂ መረጃ ያቀርባሉ። እንዲህ ያሉ ሚዲያዎች ስልክ ቁጥሮችንና ኢሜሎችን ጨምሮ አድራሻቸውን በግልጽ ያሳውቃሉ፤ ሚዲያውን ለማንቀሳቀስ የሚረዳቸው የገንዘብ ምንጭ ከየት እንደሆነ (ማስታወቂያ፣ የመንግስት በጀት፣ ከእርዳታ ድርጅቶች የሚገኝ ድጎማ ወዘተ) ይፋ ያደርጋሉ፤ ዜናዎችን ወይንም ሌሎች ይዘቶችን የሰሩ ባለሙያዎችን ማንነት በተገቢው ቦታ ያስነብባሉ። ይህም ተጠያቂነትን ለማስፈንና ተከታዮቻቸው ቅሬታ በቀላሉ እንዲያቀርቡ ያስችላቸዋል።

3. ለስህተቶች ፈጣንና ግልጽ ዕርምት ይሰጣሉ: በአንጻራዊነት ታማኝ የሆኑ ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው ለሚሰሯቸው ስህተቶች (ለምሳሌ ሀሰተኛ ወይም የተዛባ መረጃ) ፈጣንና ግልጽ የዕርምት እርምጃ ይወስዳሉ። ይህንም ተከታታዮቻቸው እንዲያውቁ ያደርጋሉ።

4. ‘ኦሪጅናል’ እና ጥራት ያላቸውን ዘገባዎችን ይሰራሉ: አሁንም በአንጻራዊነት ታማኝ የሆኑ ሚዲያዎች ‘ኦርጅናል’ የዜና ዘገባዎችን እንዲሁም ሌሎች ይዘቶችን በመስራት ይታወቃሉ፣ ለዘገባቸውም ተገቢውን ምንጭ ይጠቀማሉ። በራሳቸው ባለሙያ የተነሱ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን ከሌላ ከወሰዱም ምንጩን በግልጽ ያስቀምጣሉ። ለሆህያትና ለቁጥር ስህተቶች እንዲሁም ለቋንቋ አጠቃቀማቸው ትኩረት ይሰጣሉ።

መረጃ ለማግኘት ብለን የምንከተላቸው ሚዲያዎች ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች በትንሹ የማያሟላ ከሆነ ለሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች ሊያጋልጠን ስለሚችል ጥንቃቄ እናድርግ።

ምንጭ: News Literacy Project

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::