የምርጫ ውጤቶች እንዴት እና በማን ይገለፃሉ?

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተደረገባቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ትናንት ምሽት ተጠናቋል። የድምጽ ቆጠራና ውጤት ይፋ ማድረግ የሚጠበቁ ቀጣይ ክንውኖች ናቸው። 

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው የማህበራዊ ሚዲያ ቅኝት በአንዳንድ ገጾችና አካውንቶች ይፋዊ ያልሆኑ የምርጫ ውጤቶች ሲገለጹ ተመልክቷል። እንዲህ ያሉ ይፋዊ ያልሆኑ የምርጫ ውጤቶች ሀሠተኛና የተዛቡ እንዲሁም ለጥርጣሬና ለግጭት በር ከፋች ሊሆኑ ስለሚችሉ ከማመንዎ በፊት የምርጫ ውጤቶቹ በምርጫ ጣቢያዎች፣ በምርጫ ከልል ጽህፈት ቤቶች ወይንም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ የሆኑ መሆናቸውን ያረጋግጡ። 

በኢትዮጵያ የምርጫ ህግ መሠረት:- 

1.በምርጫ ጣቢያ የተደረገ የቆጠራ ውጤት ቆጠራው በተጠናቀቀ በአንድ ሰዓት ውስጥ በምርጫ ጣቢያው ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ወጥቶ ለህዝብ በይፋ ይገለጻል፡፡ 

2.የምርጫ ክልል የምርጫ ጽህፈት ቤቶች የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ጣቢያው እንደደረሳቸው ወይም የተረጋገጠ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር በምርጫ ክልሉ የድምጽ መስጫ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪዎች ወይም ወኪሎቻቸው በተገኙ በት ደምረው የተገኘውን ውጤት ለህዝብ ይፋ ያደርጋሉ፡፡ 

3.የምርጫ ቦርድ በአጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ክልሉ ተጠናቆ እስኪደርሰው ድረስ ከየምርጫ ክልሉ የመጣለትን የህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት የምርጫ ውጤት በጊዜያዊነት በቦርዱ ጽህፈት ቤት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሆኖም የምርጫው ይፋዊ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ካልተገለጸ ቦርዱ ጊዜያዊ ውጤቱን ይፋ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ 

4.የምርጫው ሂደት ከተጠናቀቀና አስፈላጊ መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ የተረጋገጠ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር ከምርጫው ቀን ቀጥሎ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር፤ ድምፅ የሰጡ መራጮች ቁጥር፤ ድምፅ የሰጡና ያልሰጡ የተመዘገቡ መራጮች መጠን በመቶኛ፤ የተመረጡ እጩዎች የስም ዝርዝርና የተመረጡበት የምርጫ ክልል፤ የአሸናፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች ስምና ለየምክር ቤቱ ያሸነፉትን መቀመጫ ብዛት፤ ጥቅም ላይ የዋለ፣ ያልዋለ፣ ከጥቅም ውጭ የሆነ የድምፅ መስጫ ወረቀት እያንዳንዱ እጩ በየምርጫ ጣቢያው ያገኘው የድምፅ ውጤት እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው መረጃዎች የያዘ ይፋዊ መግለጫ ያወጣል፡፡ 

5.በምርጫ ክልል ደረጃ በተገለጹ ውጤቶች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ውጤት መግለጹን እንዲዘገይ የሚያደርግ ከሆነ ይፋዊ ውጤት የሚገለጽበት ጊዜ እስከ 20 ቀን ድረስ ሊዘገይ ይችላል፡፡

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::