ጎግል ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ለመከላከል ይረዳሉ ያላቸውን አዳዲስ አገልግሎቶችን ይፋ አድርጓል! 

አዲሶቹ አገልግሎቶች የተጨመሩት በጎግል መፈለጊያ (Google Search) እና በጎግል ዜና (Google News) መገልገያዎች ላይ ነው። 

ጎግል ይፋ ካደረጋግቸው አዲስ አገልግሎቶች መካከል በመረጃ አጣሪ ተቋማት የተፈተሹ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት ያስችላል የተባለው ‘Fact Check Explorer’ ይገኝበታል (https://toolbox.google.com/factcheck/explorer)። በዚህ አገልግሎት የጎግል ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን ርዕሰ ጉዳይ በማስገባት የመረጃ አጣሪ ተቋማት ብያኔዎችን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። 

የተጣራ መረጃ ፈላጊዎች የዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ተጠቃሚ ከሆኑ ደግሞ በመረጃ አጣሪ ተቋማት የተፈተሹ መረጃዎች ከጎግል የዜና አገልግሎት ግኝቶች ጋር መሳ ለመሳ ተሰባጥረው እንዲገኙ ይሆንላቸዋል። 

ሌላኛው የተጨመረው አዲስ አገልግሎት የጎግል መፈለጊያ ተጠቃሚዎች መረጃ የሚያገኙባቸውን ድረ-ገጾች ማንነት ለማወቅ ያስችላል የተባለው ‘About this result’ የተባለው መገልገያ ነው። ይህ መገልገያ መረጃ ፈላጊዎች መረጃ ስለሚያገኙበት ድረ-ገጽ ማንነት የበለጠ እንዲያውቁ የሚያደርግ ሲሆን በዚህም ተጠቃሚዎች ለሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች የመጋለጥ እድላቸውን መቀነስ እንዲችሉ ያደርጋል ተብሏል። 

ይህን አገልግሎት ለማግኘት የጎግል መፈለጊያ በሚያመጣቸው የፍለጋ ውጤቶች ጎን የሚገኙ ሶስት ነጠብጣቦችን መጫን የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም ስለ ድረ-ገጹ ማንነት የሚገልጹ መረጃዎችን ያሳያል። 

ጎግል ወደ ትግበራ ካስገባቸው አዲስ አገልግሎቶች ሌላኛው በዜና ተቋማት በስፋት የተጠቀሰን ‘ኦርጅናል’ የመረጃ ምንጭ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ማግኘት ያስችላቸዋል የተባለው ‘Highly Cited’ የተሰኘ መገልገያ ነው። ይህ አገልግሎት በጎግል መፈለጊያ አልጎሪዝም አሰራር ምክንያት የሚዋጡ አካባቢያዊ የመረጃ ምንጮች እይታ እንዲኖራቸው በማድረግ ተጠቃሚዎችን ‘ከኦርጅናል’ የመረጃ ምንጮች ጋር ያገናኛል ተብሏል። ይህም መረጃ ፈላጊዎች የበለጠ አውድ እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን ‘ኦርጅናል’ የመረጃ አሰራጮች የተሻለ እይታ እንዲኖራቸው በማድረግ እንዲበረታቱ እንደሚያደርግ ጎግል ገልጿል። 

መረጃ ፈላጊዎች ‘ኦርጅናል’ የመረጃ ምንጮችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉም ወደ ምንጮቹ በሚያመራው  ማስፈንጠሪያ ጎን ‘Highly Cited’ የሚል ጽሁፍ እንዲነበብ ይሆናል። 

እንዲሁም ሰበር ዜና ወይም በበቂ ሃቅ ያልተደገፈ ርዕሰ ጉዳይ መነጋገሪያ በሚሆንበት ወቅት መረጃ ፈላጊዎች በቂ መረጃ ይፋ እስከሚሆን በትዕግስት እንዲጠባበቁና እንዲረጋጉ የሚያበረታታ መገልገያ ጎግል ይፋ ካደርጋቸው አገልግሎቶች ይገኝበታል። አገልግሎቱ በ20 ቋንቋዎች ስራ ላይ የዋለ ሲሆን በሌሎች ቋንቋዎችም ተደራሽ እንደሚሆን ጎግል አስታውቋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::