የአርብ ሚድያ ዳሰሳ

1. መሠረታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ 20 የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ባለፈው ማክሰኞ “ግልጽ ጥሪ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት” በሚል ርዕስ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል። የሲቪል ማኅበራቱ በደብዳቤያቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የሀሠተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ እያስከተ ያለው ጉዳት ይገኝበታል። ማህበራቱ ግልጽ ጥሪ ካቀረቡላቸው መካከል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል። 

2. የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራች የሆኑት ቢል ጌትስ እርሳቸውን የተመለከቱ የሴራ ትንተናዎች (Conspiracy Theories) በጣም እንደሚገርሟቸውና ብሎም እንደሚያስቋቸው በትናትናው ዕለት ከቢቢሲ ጋር ባደርጉት ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። ቢል ጌትስ ሴራ የሚተነትኑ ግለሰቦች “በክትባቶች አማካኝነት ቢል ጌትስ ይከታተለናል” ብለው ማመናቸው “እብደት ነው” ያሉ ሲሆን “ለምን ይህን አደርጋለሁ?” በማለት ሲጠይቁ ተደምጠዋል። ህይወት አድን የሆኑ ክትባቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ቢሊዮን ዶላሮችን ማፍሰሳቸውን የሚናገሩት ጌትስ ከዚህም የማገኘው አንዳች ትርፍ የለኝም ብለዋል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንገድ ላይ የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ሰዎች “ትከታተለናለህ” በማለት ያልተገባ ነገር እንደሚናገሯቸውም በመገረም ገልጸዋል። ከክትባቶች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ በርከት ያሉ የሴራ ትንታኔዎች በተደጋጋሚ በመረጃ አጣሪዎች ውድቅ መደረጋቸው ይታወቃል።  

3. የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የመሪነት ሚና ሊጫወት እንደሚገባ “ቡድን 77” በመባል የሚታዎቁ አገሮችንና ቻይናን በመወከል ፓኪስታን መጠየቋን ሬዲዮ ፓኪስታን ዘግቧል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፓኪስታን ቋሚ ተወካይ ሙኒር አክራም ባለፈው እሮብ ለድርጅቱ የኮሚኒሽን ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት አቤቱታ የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ በተለይም አዳጊ በሆኑ አገሮች ላይ እያደረሰ ነው ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግር አትተዋል። 

4. የአሜሪካ መንግስት ያቋቋመውን አዲሱን የሀሰተኛ መረጃ ተመልካች ቦርድ አስፈላጊነት ለማስረዳት በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት እሮብ ለት የቀረቡት የሀገር ውስጥ መስሪያ ቤቱ ሴክሬታሪ አሌያንድሮ ማዮርካ ከሪፐብሊካን ወገን ከሆኑ የምክር ቤቱ አባላት የሰላ ትችት ማስተናገዳቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። ተችዎቹ የሀሰተኛ መረጃ ተመልካች ቦርዱ ከሀገሪቱ ህገ-መንግስት እንደሚጣረስና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሊጋፋ ይችላል የሚል ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል። ሴክሬታሪ ማዮርካ በአንጻሩ የቦርዱ መቋቋም ያለው ጠቀሜታ አጽኖት ሰጥተው ያስረዱ ሲሆን የአማካሪነት ሚና ብቻ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ቦርዱ ፍልሰትን፣ የሩሲያና ዩክሬንን ጦርነት እንዲሁም ምርጫን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የባይደን አስተዳደር የሀሰተኛ መረጃ ተመልካች ቦርድ ማቋቋሙ በይፋ የታወቀው ቦርዱን እንዲመሩ የተሾሙት ኒና ጃንኮዊዝ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በትዊተር ገጻቸው ለጭምጭምታው ምላሽ ከሰጡ በሗላ ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::