የአርብ ሚድያ ዳሰሳ 

1. አለም አቀፉ የፖሊስ ህብረት (ኢንተርፖል) በሳይበር ወንጀል የሚጠረጠርን ቡድን ዋና መሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ዕረቡ እለት አስታውቋል። የወንጀል ቡድኑ ሽንገላን (phishing) እና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም በግለሰቦችና በድርጅቶች ላይ የኢንተርኔት ማጭበርበር ይፈጽም ነበር ተብሏል። የ37 ዓመቱን ናይጀሪያዊ ተጠርጣሪ ለመያዝ ከናይጀሪያ ፖሊስ የሳይበር ቡድን ጋር መቀናጀቱን የገለጸው ኢንተርፖል አራት ህጉራትን ያካለለ ኦፕሬሽን መከወኑን አብራርቷል። ኢንተርኔትን በመጠቀም የሚደረጉ ማጭበርበሮች በሀገራችን እየጨመሩ መምጣቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጥምር ግብረ ኃይል ባለፈው ሳምንት ማስታወቃቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ቼክ ድርጊቱን በተመለከተ በርከት ያሉ የማጣራትና የማንቃት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱም ይታወቃል። 

2. የዝንጀሮ ፈንጣጣ (monkeypox) ስለተባለው በሽታ ዘገባ የሚሰሩ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ሚዲያዎች የቆዩና ጥቁር አፍሪካውያንን የሚያሳዩ ፎቶዎችን መጠቀማቸው አግባብ አይደለም ሲል መቀመጫውን ናይሮቢ፣ ኬንያ ያደረገው የአፍሪካ ፎሬን ፕሬስ አሶሴሽን በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ ቅሬታውን አሰምቷል። አሶሴሽኑ በሽታው በሰሜን ንፍቀ ክበብ በሚገኙ ሀገሮች በተከሰተበት ሁኔታ እንዲህ ያሉ ፎቶዎችን መጠቀም ጥቁር ቀለም ባለቸው ሰዎች አንጻር የቀጠለውን መገለልና አሉታዊ ዕይታ የሚያስቀጥል ነው ሲል ተችቶታል። ይህን አይነቱን የፎቶ አጠቃቀም በርከት ያሉ ሰዎች በተለይ በትዊተር ሲተቹ የተስተዋለ ሲሆን አሰራሩ ባለፉት ጥቂት ቀናት መሻሻል ማሳየቱን ኢትዮጵያ ቼክ ታዝቧል። 

3. “በሀሠተኛ መረጃ አሰራጭነት መፈረጅ” የጋዜጠኞች ዋና ተግዳሮት መሆኑን ሲሲዮን የተባለ ዓለም አቀፍ የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ተቋማ  ይፋ ያደረገው ዓመታዊ ጥናት ጠቆመ። ተቋሙ በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገው ይህ ጥናት 37% የሚሆኑ ጋዜጠኞች በሀሠተኛ መረጃ አሰራጭነት የሚደርስባቸውን ፍረጃ መከላከልና ታማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ለመቀጠል የሚያደርጉት ጥረት የሙያቸው ዋና ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል። ሲሲዮን የ2022 ዓ.ም ዓለም አቀፍ  የሚዲያ ሁኔታ የሚዳስሰውን ን ጥናት ለመስራት በ17 ሀገሮች የሚገኙና ከ2,000 በላይ በሆኑ የሚዲያ ተቋማት የሚሰሩ 3,800 ጋዜጠኞችን በጥናቱ አካቷል። 

4. በመጭው መስከረም ሊደረግ ቀን የተቆረጠለትን የብራዚል አጠቃላይ ምርጫ ከሀሠተኛና የተዛባ መረጃ የጸዳ ለማድረግ ቴሌግራምና የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል። በስምምነቱም ቴሌግራም በፕላትፎርሙ የሚሰራጩ ሀሠተኛ መረጃዎች የመለየትና ዕርምጃ የመውሰድ፣ ምርጫውን የተመለከቱ ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት ቻት-ቦት መክፈት እንዲሁም ከፍርድ ቤቱ ጋር ግንኙነት መመስረት የሚሉ ተካተውበታል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከወራት በፊት ቴሌግራም መተግበሪያ በብራዚል ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል ዕቀባ ጥሎ እንደነበር ይታወሳል። 

5. ዩትዩብ የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ ሀሠተኛና የተዛባ መረጃ አሰራጭተዋል ያላቸውን 9,000 ቻናሎችን መዝጋቱንና ከ70,00 በላይ ቪዲዮዎችን መሰረዙን ዘጋርዲያ ጋዜጣ በሳምንቱ መጀመሪያ አስነብቧል። ዩትዩብ ስለተዘጉት ቻናሎች ማንነትና ስለቪዲዮዎቹ ይዘት ዝርዝር መረጃ አለመስጠቱንም ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::