የአርብ ሚድያ ዳሰሳ 

  1. በቲክቶክ እየተሰራጩ ያሉ የጥላቻ መልዕክቶችና ሀሠተኛ መረጃዎች በመጭው ነሀሴ ወር ሊደረግ በታቀደው የኬኒያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ቀውስ ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው ሞዚላ ፋውንዴሽን በሳምንቱ አጋማሽ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። ሞዚላ ፋውንዴሽን ስጋቱን የገለጸው በቅድመ ምርጫ ወቅት በቲክቶክ በስፋት የታዩ 130 ናሙና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ከመረመረ በኃላ መሆኑን በሪፖርቱ አስነብቧል። ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ በግልጽ የቲክቶክን ፖሊሲዎች የሚጥሱ ቢሆኑም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ምንም እርምጃ አለመውሰዱም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
  1. ከመስከረም እስከ ሰኔ ባሉት ዘጠኝ ወራት5 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶች ሰለባ መሆናቸውን ‘PIXM’ የተባለ የሳይበር ደህንነት ተቋም በትናንትናው ዕለት ባወጣው ሪፖርት አስነብቧል። የማጭበርበርና የማታለል ድርጊቶቹ በተለይም በፌስቡክ ሜሴንጀር በኩል በሚላኩ ማስፈንጠሪያዎች (links) አማካኝነት መሆኑን በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በድርጊቱም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በአጭበርባሪዎችና በአታላዮች እጅ መግባቱ ተገልጿል።
  1. ህንድ እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዩትዩብ ያሉ ግዙፍ የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በይዘት አስተናባሪዎች (content moderaters) አማካኝነት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች የሚመለከት የይግባኝ ሰሚ ፓናል ለማቋቋም ማቀዷን የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል። ፓናሉ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በሚወስዷቸው እርምጃዎች አንጻር ቅሬታ ያለው ዜጋ ይግባኝ የሚልበት ነው። የህንድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኤሌክትሮኒክስ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ ፓናሉ ግዙፍ ካምፓኒዎች የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ መብት እንዳይጋፉ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጿል።
  1. ትዊተርን ለመግዛት ቅድመ ስምምነት ላይ የደረሰው ቢሊየነሩ ኢሉን መስክ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴው የስፓም አካውንቶችን ምጣኔ እንዲያሳውቀው ሰኞ ዕለት በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል። ኢሉን መስክና ትዊተር ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ተጠቃሚዎች ምን ያህሉ ቦቶች ናቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ከስምምነት አልደረሱም። ትዊተር የቦቶች ምጣኔ ከ5% አይበልጥም ሲል ኢሉን መስክ በበኩሉ ቁጥሩ ከዚያ ከፍ ሊል እንደሚችል በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል።
  1. ፌስቡክ በኢትዮጵያ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚስተጋቡ የጥላቻ ንግግሮችን የመለየት አቅሙን ለመፈተሽ ፈትኜው በተደጋጋሚ ወድቋል ሲል ግሎባል ዊትነስ የተባለ ተቋም በትናትናው ዕለት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስነብቧል። የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ በበኩሉ በግሎባል ዊትነስ ሪፖርት የተጠቀሱት የጥላቻ ንግግሮች ለፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከመድረሳቸው በፊት እንዲሰረዙ ተደርገዋል በማለት ለኢትዮጵያ ቼክ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::