የአርብ ሚድያ ዳሰሳ

  1. ናይጄሪያ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ህግ እንዲመዘገቡ፣ ታክስ እንዲከፍሉ፣ የሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ስርጭትን እንዲቆጣጠሩ የሚያስገድድ ረቂቅ ደንብ በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ አድርጋለች። ሰኞ ዕለት በናይጄሪያ ብሔራዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ድረ-ገጽ ይፋ የተደረገው ረቂቅ ደንብ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ጎግልና ቲክቶክ በናይጄሪያ እንዲመዘገቡና ወኪል እንዲያስቀምጡ እንዲሁም ታክስ እንዲከፍሉ ያስገድዳል። እንዲሁም ከሀገሪቱ ህግ ጋር የሚጻረሩ ይዘቶች እንዲያስወግዱ፣ የተቀናጁ የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻዎችን፣ አደገኛና ሀሰተኛ የሆኑ አካውንቶችን ለመንግስት እንዲያሳውቁ ይደነግጋል። ረቂቅ ደንቡ የናይጄሪያ ዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
  1. የጃፓን ፓርላማ በኦላይን የሚሳደቡ ሰዎችን በእስርና በገንዘብ የሚቀጣ ህግ ሰኞ ዕለት ማጽደቋን ጃፓን ታይምስ ድረ-ገጽ ዘግቧል። በህጉ መሰረት የኦላይን መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚሳደቡ አካላትን እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም እስከ 300,000 የጃፓን የን በሚደርስ ገንዘብ ይቀጣል። ህጉ የጸደቀው የ22 ዓመቷ ዝነኛ የቴሌቪዥን ሾው አቅራቢና የሪስሊንግ ተወዳዳሪ ሃና ኪሙራ እራሷን ያጠፋችው በማህበራዊ ሚዲያዎች ከደረሰባት ስድብና ጫና በኃላ መሆኑ መነጋጋሪያ መሆኑን ተከትሎ ነው። ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ተሟጋቾች ህጉ አሉታዊ ተጽኖ እንዳይኖረው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
  1. ከሠላሳ በላይ ግዙፍ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የሀሠተኛና የተዛቡ መርጃዎችን ስርጭት ለመቀነስ ያስችላል የተባለን አዲስ ደንብ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ተፈራርመዋል። በህብረቱ የተረቀቀውን አዲስ ደንብ ከተፈራረሙት ኩባንያዎች መካከል ጎግል፣ ሜታ፣ ትዊተር፣ ቲክቶክና ማይክሮሶፍት ይገኙበታል። በሳምንቱ አጋማሽ ለፊርማ የቀረበው ደንብ ካምፓኒዎቹ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ይዘታቸውን በክፍያ እንዳያስተጋቡ፣ ሀሠተኛና ቦት አካውንቶችን እንዲቆጣጠሩ፣ እንዲሁም ለሌሎች አሉታዊ ድርጊቶች ትኩረት እንዲሰጡ ያበረታታል። ቴሌግራም፣ አፕልና አማዞን ደንቡን ካለፈረሙት መካከል ይገኙበታል።
  1. የዩትዩብ ቻናል አሰናጆች ቪዲዮ ከጫኑ በኃላ ስህተቶችን በቀላሉ ማረም እንዲችሉ የሚያስችል አገልግሎት መጀመሩን ካምፓኒው ይፋ አድርጓል። ‘እርማቶች’ (corrections) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አገልግሎት የቻናል አሰናጆች በጫኑት ቪዲዮ ላይ የተሳሳተ መረጃ ወይም ሌላ መስተካከል ያለበት ክፍል ካለ ማወረድ ሳያስፈልጋቸው እርማት መስጠት ያስችላል። ይህም ከዚህ ቀደም የተጫኑ ቪዲዮዎች ታርመው እንደገና በሚጫኑበት ወቅት የሚያጋጥመውን የእይታ መረጃና የኮሜንት መሰረዝን ያስቀራል ተብሏል።
  1. ወላጆች የታዳጊዎችን የኢንስታግራም አጠቃቀም መቆጣጠር የሚያስችላቸውን አገልግሎት መጀመሩን ሜታ አስታውቋል። አገልግሎቱ ወላጆች የታዳጊዎችን የመጠቀሚያ ጊዜ ርዝመት እንዲመጥኑና ሌሎች ክንውኖችን እንዲቆጣጠሩ ያስችላል ተብሏል። ኢንስታግራም በተለይ በታዳጊዎች ላይ እራስን እስከማጥፋት በሚያደርሱ የስነልቦና ጫናዎችን መቆጣጠር አልቻለም በሚል ሲተች መቆየቱ ይታወቃል። አገልግሎቱ በዩናይትድ ስቴትስና በተወሰኑ የአውሮፓ አገሮች መሰጠት የጀመር ሲሆን የፈረንጆች ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት በመላው አለም ተደራሽ እንደሚሆን ተገልጿል።
  1. በመጨረሻም፣ ዋትስአፕ አማርኛንና አፋን ኦሮሞን ከመተግበሪያው የቋንቋ አማራጮች ውስጥ ማስገባቱን በሳምንቱ አጋማሽ አስታውቋል። በዚህም የአንድሮይድ መገልገያ ተጠቃሚዎች የቋንቋ ምርጫቸውን አማርኛ ወይም አፋን ኦሮሞ ላይ በማድረግ መጠቀም እንደሚችሉ ዋትስአፕ ገልጿል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::