የአርብ የሚድያ ዳሰሳ

ሰኔ 24/2014

1. ‘ፊያስበተባለ የኦንላይን ማጭበርበሪያ ድርጊት ገንዘባቸውን ያጡ ሰዎች ለሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በዛሬው ዕለት ጥሪ ማቅረቡን ኢቢሲ ዘግቧል። በፊያስተጭበረበሩ ሰዎች ባደረሱት ጥቆማ መሰረት የተለያዩ የክፍያ መንገዶችን በመጠቀም የሰዎችን ገንዘብ የሰበሰቡ አካላትን ሁኔታው እስከሚጣራ ድረስ የባንክ ሂሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ የሚደረግበት አግባብ እንደሚኖር የገለጸው አገልግሎቱ ሆኖም አጠቃላይ የወንጀል ምርመራ ሂደቱ ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ጉዳዩ ተጣርቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝርዝር መረጃዎችን ማቅረብ እንደማይቻልም አስታውቋል። ኢትዮጵያ ቼክ በፊያስ ዙርያ የማሳሰብያ መልዕክቶችን ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል። 

2. ከአራት ወራት በኋላ በኳታር አስተናጋጅነት በሚደረገው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ወቅት ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በተጫዋቾች፣ በአሰልጣኞች፣ በዳኞችና በተመልካቾች አንጻር የሚሰነዘሩ የጥላቻ መልዕክቶችን ለመቆጣጠር ዝግጅት ማድረጉን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (FIFA) አስታውቋል። ፊፋ በገለልተኛ አካል አስጠናሁት ያለውን ሪፖርት ይፋ ያደረገ ሲሆን በ2020 የአውሮፓ ዋንጫና በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ተጫዎቹች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የጥላቻ ንግግር ሰላባ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል። በሁለቱ ውድድሮች የግማሽ ፍጻሜና የዋንጫ ጨዋታ ወቅት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተላለፉ 400,000 መልዕክቶች ላይ በተደረገ ጥናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የውድድሮቹ ተሳታፊ ተጫዋጮች ዘረኝነትን ጨምሮ የጥላቻ ንግግር ሰላ በመሆናቸው በሪፖርቱ ተካቷል። ፊፋ ይህ ድርጊት በኳታሩ የዓለም ዋንጫ እንዳይደገም ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር (FIFPRO) ጋር በመቀናጀት ሰፊ የማህበራዊ ሚዲያ ቅኝትና ክትትል በማድረግ የሚጋሩ የጥላቻ መልዕክቶች እንዳይታዩ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል። 

3. በፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉ ሰዎች በስርጭቱ ወቅት ከተከታታዮች የሚሰጡ ግብረመልሶችን የሚያስተናብርና የሚቆጣጠር ሰው (Community Manager) መመደብ የሚችሉበትን አሰራር መጀመሩን ሜታ አስታውቋል። ይህም በቀጥታት ስርጭት የሚገባው ሰው ትኩረቱን ማስተላለፍ በፈለገው መልዕክት ላይ እንዲያተኩር እንዲሁም በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ዘለፋን ጨምሮ ተገቢ ያልሆነ መልዕክቶችን የሚያሰፍሩ ታዳሚዎችን ለመቆጣጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል። 

4. የዩናይትድ ስቴትስ ፌድራል ኮሚኒኬሽን ኮሚሽን አፕልና ጎግል ቲክቶክን ከአፕስቶር (App Store) እና ከጎግልፕሌይ Google Play) እንዲያወርዱ ጠይቋል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር የሆኑት ብሬንዳን ካር ቅዳሜ ዕለት በጻፉትና በትዊተር ገጻቼው ባጋሩት ባለ አራት ገጽ ደብዳቤ ቲክቶክ የአሜሪካዊያን ደንበኞቹን መረጃ ለቻይና ገዥ ፓርቲ አሰልፎ ይሰጣል የሚል ስጋታቸውን በማብራራት ካምፓኒዎቹ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ከአፕስቶርና ከጎግል ፕሌይ እንዲያወርዱት ጠይቀዋል። 

5. በፌስቡክ ፐብሊክ ግሩፖች አባል ያልሆኑ ሰዎች በግሩፕ አስተናባሪዎች (Group Admins) ፈቃድ ብቻ መልዕክት የሚለጥፉበትና አስተያየት የሚሰጡበትን አሰራር ከመጭው ሳምንት መጀምሪያ ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚያስገባ ፌስቡክ አስታውቋል። በተጨማሪም በአዲሱ አሰራር ሰዎች ያለ ግሩፕ አስተናባሪዎች ይሁንታ ፐብሊክ ግሩፖችን መቀላቀል የሚችሉም ይሆናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::