የአርብ ሚድያ ዳሰሳ 

1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማህበራዊ ድረ-ገጽን በመጠቀም የተለያዩ የስራ ሀላፊዎችን መልካም ስምና ክብር አጉድፏል ያለውን ግለሰብ በአንድ አመት ከአምስት ወር እስራት መቅጣቱን የድሬዳዋ ፖሊስ አስታውቋል። አብዮት አየለ የተባለው ግለሰብ በእስራት የተቀጣው በተለያዩ ወቅቶች አምስት የስራ ሀላፊዎችን “ክብር ወይም መልካም ስም ለማጉደፍ በማሰብ” ‘Abyot Ayele’ በማለት በከፈተው የፌስቡክ ገፅ የግል ተበዳዮችን ፎቶ በመለጠፍና አስነዋሪ ስድብ ጽፎ በማሰራጨቱ መሆኑ ተገልጿል። ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ሊያስተላልፍ የቻለው የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 13/3/ ላይ የተመለከተውን ተላልፎ በመገኘቱ መሆኑን ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል። 

2. ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጎግል በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የትርጉም አገልግሎት መስጠት መጀመሩን እረቡ ዕለት አስታውቋል። ጎግል ከኦሮምኛና ከትግርኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ ሌሎች 22 ቋንቋዎችን ወደ ጎግል መተርጎሚያ ስርዐት ያስገባ ሲሆን ይህም በጎግል መተርጎሚያ ስርዐት ውስጥ የተካተቱ ቋንቋዎችን ቁጥር 133 አድርሶታል። ወደ ስርዐቱ የገቡት ቋንቋዎች ትርጉም ፍጹም አለመሆኑን የገለጸው ጎግል በጊዜ ሂደት እንደሚሻሻል ያለውን ተስፋ ገልጿል። አማርኛ ቋንቋ ከአመታት በፊት ወደ ጎግል መተርጎሚያ ስርዐት መካተቱ ይታወቃል። 

3. ትዊተር የተባዙ ወይም በእንግሊዘኛው “Copypasta” በመባል የሚታወቁ ይዘቶችን በሚያሰራጩ ተጠቃሚዎቹ ላይ ተደራሽነታቸውን ከመቀነስ እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን በሳምንቱ አጋማሽ አስታውቋል። ይህ እርምጃ የትዊተር ተጠቃሚዎች ታማኝና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ እንዲሁም የፕላትፎርሙን ስነምህዳር ጤንነት ለመጠበቅ እንደሚረዳ ትዊተር ያለውን እምነት ገልጿል። ድምጻቸውን ለማሰማት በዘመቻ መልክ ወደ ትዊተር ጎራ የሚሉ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን የተባዙ ወይም “Copypasta” ይዘቶችን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ ይታያል። 

4. ጎግል ደንበኞቹ የግል መረጃዎቻቸው በጎግል መፈለጊያ ውጤቶች (Google Search Results) ላይ እንዲሰረዝ ማድረግ የሚችሉበትን አዲስ መተግበሪያ በቅርቡ ስራ ላይ እንደሚያውል እረቡ እለት አስታውቋል። አዲሱ መተግበሪያ ግለሰቦች እንደ ስልክ ቁጥር፣ ኢሜል፣ የመኖሪያ ቤት አድራሻ ያሉ የግል መረጃዎቻቸው በጎግል መፈለጊያ ውጤቶች ላይ እንዲሰረዝ ከፈለጉ በቀላሉ ሪፖርት ማድረግ ያስችላቸዋል ተብሏል። አዲሱ መተግበሪያ ስራ ላይ እስከሚውል ደንበኞቹ የግል መረጃዎቻቸውን ለማሰረዝ በጎግል ሰፖርት በኩል ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉም ተገልጿል። 

5. የትዊተር ኩባንያ ሽያጭ ሂደት በጊዜዊነት እንዲቆም መደረጉን ካምፓኒውን ለመግዛት የተስማማው ቢሊየነሩ ኢሉን መስክ ዛሬ ማለዳ ላይ አስታውቋል። ኢሉን በትዊተር ገጹ ባሰፈረው አጭር መልዕክት የግዥ ሂደቱ እንዲቆም የተደረገው ካፓኒው የስፓም አካውንቶችን ቁጥር ያሰላበትን ሂደት ዝርዝር ለማወቅ መሆኑን ጠቅሷል። ትዊተር በየዕለቱ ወደ ፕላትፎርሙ ጎራ ከሚሉ ለማስታወቂያ ብቁ ከሆኑ ተጠቃሚዎች መካከል ሀሰተኛና ‘ስፓም’ አካውንቶችን የሚጠቀሙት ቁጥር ከ5% አይበልጥም የሚል መረጃ ከሳምንት በፊት አውጥቶ ነበር።  ሀሰተኛና ‘ስፓም’ አካውንቶችን ከፕላትፎርሙ ማጽዳት በትዊተር ለመተግበር ካቀዳቸው ተግባራት ቀዳሚው መሆኑን መስክ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::