የአርብ የሚድያ ዳሰሳ 

1. ኬንያ ፌስቡክን ለመዝጋት የሰጠችው ማስጠንቀቂያ ተግባር ላይ እንደማይውል የሀገሪቱ የኮሚኬሽን፣ ኢንፎርሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስታውቀዋል። የኬኒያ ብሔራዊ የውህደት ኮሚሽን በመጭው ሳምንት በሀገሪቱ በሚደረገው ምርጫ አንጻር የሚሰራጩ የጥላቻ መልዕክቶችን በመቆጣጠር ረገድ የሚጠበቅበትን እየተወጣ አይደለም ያለውን ፌስቡክ በሰባት ቀናት ውስጥ ቁጥጥሩን ጠበቅ እንዲያደርግ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። ሆኖም የኬኒያ የኮሚኬሽን፣ ኢንፎርሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትሩ ጆ ሙቹሩ ኮሚሽኑ ይህን የማድረግ ስልጣን እንደሌለውና መንግስታቸውም ፌስቡክን የመዝጋት እቅድ እንደሌለው ሰኞ እለት ለሮይተርስ ተናግረዋል። በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍሬድ ማቲያንጊ የኮሚሽኑ ማስጠንቀቂያ መንግስታቸውን እንደማይወክልና የኬኒያውያን ሀሳብን የመግለጽ መብት የሚጻረር ተግባር እንደማይፈጸም በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። 

2. ዩትዩብ በተለይም በናይጄሪያ ላልተገባ አላማ እንዳይውል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጎግል አስታውቋል። ጎግል ይህን ያስታወቀው የናይጄሪያ መንግስት ማክሰኞ እለት በፕላትፎርሙ አንጻር ትችት አዘል ክስ ካቀረበ በኃላ ነው። የናይጄሪያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሊያ ሞሐመድ መንግስታቸው የሀገሪቱን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አደገኛ ካሏቸው መልዕክቶች ለመጠበቅ እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት የሚደረገውን ምርጫ ከሠተኛ መረጃዎች ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።    

3. የፌስቡክና የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ካልተወዳጇቸው ወይም ከማይከተሏቸው አካውንቶች በጥቆማ መልክ (recommendation) የሚመጡ ይዘቶችን የመመልከት ዕድላቸው በመጭው የፈረንጆች ዓመት በእጥፍ እንደሚጨምር ሜታ አስታውቋል። የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ እንደገለጸው በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ፕላትፎርሞች በጥቆማ መልክ ለተጠቃሚዎች እንዲታዩ የሚደረጉ ይዘቶች ድርሻ 15% ገደማ ሲሆን በመጭው ዓመት ድርሻው በእጥፍ ይጨምራል። 

4. ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ማዕከል ያደረጉ 9,000 የሚጠጉ የሳይበር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ላይ መሞከራቸውን እና ከዚህም ውስጥ 97 በመቶ የሚሆኑትን ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታውቋል። የአስተዳደሩ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ  ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢመደአ በ2014 በጀት አመት ከተቃጡ 8,985 የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 45 ከመቶ የሚሆኑት ቁልፍ የሀገሪቱን መሰረተ ልማት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውም ጠቅሰዋል። የጥቃት ሙከራዎች ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የፋይናንስ ተቋማት፤ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የመንግስት የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጤና ተቋማትና የግል ድርጅቶችም ይገኙበታል ብለዋል ፡፡ 

✅️ በዚህ ሳምንት ያቀረብናቸው መረጃዎች እና የቴሌራም ሊንኮቻቸው:- 

– በሰኞ መልዕክታችን የማህበራዊ ሚድያ ገፆችን፣ አካውንቶችን እና ቻናሎችን እንዴት ማረጋገጫ ማሰጠት እንደሚቻል (verification ማስገኘት እንደሚቻል) በአፋን ኦሮሞ ቃኝተናል: https://t.me/ethiopiacheck/1447 

– እንዲሁም ከሰኞ መልዕክት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ቪዲዮዎችን በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች አጋርተናል:-

https://t.me/ethiopiacheck/1453

https://t.me/ethiopiacheck/1455

https://t.me/ethiopiacheck/1454 

– ሰኞ ዕለት ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተገናኘ ከአውድ ውጭ የቀረበ ፎቶ አጣርተናል: https://t.me/ethiopiacheck/1450 

– እሮብ ዕለት የበላይነህ ክንዴ ግሩፕን የንግድ ምልክትና ስያሜ በመጠቀም የተከፈተ ሀሠተኛ የቴሌግራም ቻናል አጋልጠናል: https://t.me/ethiopiacheck/1452

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::