የአርብ የሚድያ ዳሰሳ 

1. የማህበራዊ ሚድያ ኩባንያዎች ቲክቶክ እያስመዘገበ ያለው ከፍተኛ እድገት እንዳሳሰባቸው እየተነገረ ነው። የዛሬ አራት አመት ስራ ሲጀምር ብዙም ትኩረት አግኝቶ ያልነበረው እና ዋና መቀመጫውን ቻይና ያደረገው ቲክቶክ አሁን ላይ ያለው የተጠቃሚዎች ቁጥር አንድ ቢልዮን እንደደረሰ ታውቋል። እንደ ኢንስታግራም እና ዩትዩብ ያሉ አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያዎችም የቲክቶክን የቪድዮ አቀራረብ ኮፒ በማድረጋቸው ነቀፋ እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። በቅርብ ወራት ቲክቶክ ያለው የተጠቃሚዎች ቁጥር 1.8 ቢልዮን ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል።

2. የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ ባለፉት ሶስት ወራት የማስታወቂያ ገቢ ቅናሽ እንዳጋጠመው ታውቋል፣ ይህም ድርጅቱ ከአመት-አመት ያጋጠመው የመጀመርያው የገቢ መቀነስ ነው ተብሏል። ባለፉት ሶስት ወራት የሜታ ገቢ 28.8 ቢልዮን ዶላር እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ይህም ከባለፈው ሶስት ወር የ1% ቅናሽ አለው። ይሁንና ሜታ የተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ እንዳላጋጠመው አብሮ ተገልጿል ብሮ ቴክ ክረንች ዘግቧል። 

3. በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአለፋ ወረዳ ነዋሪዎች አንዳንድ የፌስቡክ ገፆች ወረዳውን በተመለከተ ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ እንደሆነ ባሳለፍነው ሳምንት ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት እነዚህ ገፆች ያልተከሰቱ ድርጊቶችን እንደተከሰቱ አርጎ በማቅረብ የማህበረሰቡ ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ አፋጣኝ እርምጃ እና ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል ብሎ የወረዳው ኮሚኒኬሽን ዘግቧል። 

4. ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ለአዲስ አበባ ወረዳ 11 ፖሊስና የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ስልጠና መሠጠቱ ባሳለፍነው ሳምንት ተገልጿል። በዚሁ ወቅት የማህበራዊ ሚድያ መስፋፋትን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የሃሰት መረጃ ስርጭት በብዙ ሀገራት፣ ተቋማት፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች ላይ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችን ማስከተሉ ተገልፆ ፖሊስ በዚህ ዙርያ ከፍ ያለ ንቃት ኖሮት የክትትል ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል። 

✅️ በዚህ ሳምንት ያቀረብናቸው መረጃዎች እና የቴሌራም ሊንኮቻቸው: 

– በሰኞ መልዕክታችን የማህበራዊ ሚድያ ገፆችን፣ አካውንቶችን እና ቻናሎችን እንዴት ማረጋገጫ ማሰጠት እንደሚቻል (verification ማስገኘት እንደሚቻል) ቃኝተናል: https://t.me/ethiopiacheck/1431 

– ማክሰኞ እለት ኬንያ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ላይ ቅሬታ አስገብታ እንደነበር ተደርጎ በአንድ ሚድያ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን አረጋግጠናል: https://t.me/ethiopiacheck/1432 

– በዚሁ ቀን በአትሌት ሲፋን ሀሰን ስም እና ምስል ተመሳስሎ የተከፈተ አንድ የፌስቡክ ገፅ ያጋራውን ሀሰተኛ መረጃ አረጋግጠናል: https://t.me/ethiopiacheck/1434 

– አሁንም ማክሰኞ እለት አትሌት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ ዘመናዊ መኪና እንደተሸለመች የሚገልፅ ሀሰተኛ መረጃን አረጋግጠናል: https://t.me/ethiopiacheck/1435 

– እሮብ እለት የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት የተለጠፈበት ድረ-ገፅ እየሰራ እንዳልሆነ በደረሰን ጥቆማ መሰረት የከተማውን ትምህርት ቢሮ አነጋግረን መረጃ አቅርበን ነበር: https://t.me/ethiopiacheck/1436 

– ትናንት ሀሙስ የትዊተር ማረጋገጫ ምልክት (verification badge) እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በአማርኛ ቋንቋ የተሰራ ቪድዮ አጋርተናል: https://t.me/ethiopiacheck/1437 

– በዛሬው እለት ደግሞ በትግርኛ (https://t.me/ethiopiacheck/1438) እና በአፋን ኦሮሞ (https://t.me/ethiopiacheck/1439) የቀረቡት የትዊተር ማረጋገጫ ማግኛ ሂደቶች ቀርበዋል። 

መልካም ቀን!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::