የአርብ ሚድያ ዳሰሳ 

1. ትዊተር በቀውስ ወቅት የሚኖርን የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ያለመ ፖሊሲ በትናትናው ዕለት ይፋ አድርጓል። “የቀውስ ወቅት የተዛባ መረጃ ፖሊሲ” (Crisis Misinformation Policy) በሚል ስያሜ ትናንት ይፋ የሆነው ይህ ፖሊሲ ትዊተር ኢትዮጵያን፣ አፍጋኒስታንና ህንድን በተመለከተ እየሰራው ያለውን ስራ እንደሚያጎለብት ገልጿል። አዲሱ ፖሊሲ በቀውስ ጊዜ የሚሰራጩ የሀሠተኛ መረጃዎችን ተደራሽነት የሚገታ ሲሆን በተለይም አሰራጩ አካውንት ቬሪፋይድ ከሆነ፣ ከመንግስት ጋር ንክኪ ያለው ሚዲያ ከሆነ እንዲሁም የመንግስት ይፋዊ አካውንት ከሆነ በተጠቃሚዎች ከመነበቡ በፊት በማስጠንቀቂያ አዘል ሽፋን ስር እንደሚቀመጥ አብራርቷል። የሀይል ዕርምጃን፣ ከድንበር ጋር የተያያዙ የልዕዋላዊነት መደፈርን፣ የጦር ወንጀልን፣ የዓለም አቀፍ ምላሽና ማዕቀብን ወዘተ የመለከቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መልዕክቶች በፖሊሲው የተካተቱ ናቸው። 

2. በመጪዎቹ ወራት በኬንያና በላይቤሪያ በሚደረጉ ምርጫዎች የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች የሚያደርሱትን ተግዳሮት ለመቀነስ ያግዛል የተባለ መገልገያን ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሩን የተመድ የልማት ፕሮግራም ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል። ይህ ‘iVerify’ የሚል መጠሪያ ያለው መገልገያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስንና የሰው ሀይልን በማጣመር ከምርጫ ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን በማጣራት ለህዝብ ያቀርባል ተብሏል። ‘iVerify’ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በዛምቢያ በተደረገው ምርጫ በሙከራ ደረጃ ጥቅም ላይ ውሎ አበረታች ውጤት ማሳየቱንም የተመድ የልማት ፕሮግራም አስታውሷል። መገልገያው ከምርጫ ባሻገር ያሉ ሌሎች ርዕሰ ጉዮች ላይ ጥቅም ላይ ለማዋልና ለጋዜጠኞች፣ ለመረጃ አጣሪዎችና ለተመራማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱም ተገልጿል። 

3. የናይጄሪያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ካምፓኒዎች የጥላቻ ንግግርን በመቆጣጠር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ያህል  እየሰሩ አለመሆናቸውን በመጥቀስ መውቀሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ሚንስትሩ ሌይ ሞሃመድ ወቀሳውን የሰነዘሩት ባሳለፍነው ማክሰኞ በናይጄሪያ ከፌስቡክ ተወካዮች ጋር ከተወያዩ በኋላ ነበር። ሚኒስትር ሌይ መንግስታቸው በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርብም ፌስቡክ ይህ ነው የሚባል እርምጃ አለመውሰዱን ጠቅሰዋል። 

4. የአሜሪካውን ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ከሚከተሉ 22.2 ሚሊዮን የትዊተር አካውንቶች መካከል 49.3% ያህሉ ሀሠተኛ መሆናቸውን ‘ስፓርክቶሮ’ የተሰኘ የማርኬቲንግ ኩባንያ የሠራው የኦዲት ሪፖርት ማመልከቱን ኒውስዊክ መጽሔት በሳምንቱ መጀመሪያ አስነብቧል። ስፓርክቶሮ በሀሠተኛነት የፈረጃቸው ስፓሞችን፣ ቦቶችን፣ ለፕሮፓጋንዳ የተከፈቱ አልያም መጠቀም ካቆሙ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ አካውንቶችን መሆናቸውን መጽሔቱ ጨምሮ አብራርቷል። ትዊተርን ለመግዛት የተስማማው ኢሎን መስክና ትዊተር ካምፓኒ በፕላትፎርሙ የሀሠተኛ አካውንቶችን ድርሻ በተመለከተ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል። 

5. የአሜሪካ መንግስት ከሳምንታት በፊት ያቋቋመው የሀሠተኛ መረጃ ተመልካች ቦርድ ስራ እንዲያቆም መደረጉን ዋሽንግተን ፖስት በሳምንቱ አጋማሽ አስነብቧል። ቦርዱ ባለፈው ሰኞ ስራውን እንዲያቆም የተወሰነው በተለይም ቀኝ ዘመም ከሆኑ ፖለቲከኞችና ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ከደረሰበት ከፍተኛ ትችት በኋላ መሆኑ ተገልጿል። ተቺዎች ቦርዱን ከታዋቂው ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ‘1984’ መጽሐፍ “Ministry Of Truth” ጋር ማያያዛቸውን ጋዜጣው ጠቅሷል። በተለይ ትችቱ ቦርዱን እንዲመሩ ከተሾሙት ኒና ጃንኮዊዝ አንጻር የበረታ እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት ያስነበበ ሲሆን ሃላፊዋ ማክሰኞ ዕለት መልቀቂያ ማስገባታቸውንም ጨምሮ ጽፏል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::