የአርብ ሚድያ ዳሰሳ 

1. ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የመረጃ አጣሪዎች ጉባዔ ዕረቡ ዕለት በኖርዌ ኦስሎ ከተማ ተጀምሯል። ለአራት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ መረጃ ማጣራትን የተመለከቱ ጥናቶች፣ ፓናሎች፣ በጎ ተሞክሮዎች እየቀረቡበት ሲሆን ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በአካል ተገኝተውበታል። ጉባዔውን ያሰናዳው ዓለም አቀፍ የመረጃ አጣሪዎች ትስስር (IFCN) ነው። 

2. ለቱርክ ፓርላማ የቀረበን የፀረ-ሀሠተኛ መረጃ ረቂቅ ህግን የተቃወሙ ጋዜጠኞችና የሲቪል ማህበራት አባላት ማክሰኞ ዕለት በኢስታምቡልና በሌሎች ከተሞች ሰልፍ ማድረጋቸውን የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል። አዲሱ ረቂቅ ህግ የሚዲያና የኢንተርኔት ስነ-ምህዳሩን ያቀጭጫል የሚል ፍርሃት እንዳላቸው በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፉ የቱርክ የሚዲያና የሲቪል ማህበራት መግለጻቸውም ተገልጿል። ረቂቅ ህጉ ከሶስት ሳምንታት በፊት ነበር በቱርክ ገዥ ፓርቲና አጋሮቹ አሠናጅነት ለፓርላማ የቀረበው። 

3. በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች ሰዎች ያላቸውን የርህራሄ መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ዩናይትድ ዌይ ኤንሲኤ (United Way NCA) የተባለ ተቋም በአሜሪካውያን ላይ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት አሳየ። የዳሰሳ ጥናቱ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች ሰዎችን ወደ ርህራሄ ድርቀት (empathy burnout) እንዳመራቸው የጠቆመ ሲሆን 57% አሜሪካውያን የችግሩ ሰላባ መሆናቸውን አስነብቧል። 

4. በታዳጊዎች ላይ እራስን እስከማጥፋት የሚደርስ የስነልቦና ጫና እያሳደረ ነው የሚል ክስ በተደጋጋሚ የሚቀርብበት ኢንስታግራም ዕድሜን ለማጣራት የሚችል ቴክኖሎጂን ወደ ሙከራ ማስገባቱን አስታውቋል። ኢንስታግራም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች እንደሆነ የሚጠረጥራቸውን ታዳጊዎችን የቪዲዮ ሰልፊ (video selfie) እንዲልኩ በማድረግ ለዚህ ተግባር ተብሎ በተዘጋጀ መገልገያ የዕድሜ ግመታ እንደሚከውን ገልጿል። ግመታው በዕድሜያቸውን ካስመዘገቡ በኃላ አርትዖ በሰሩ ታዳጊዎች ላይ ሲሆን ከቪዲዮ ሰልፊው በተጨማሪ መታወቂያና የጓደኛ ምስክርነት እንደሚጠየቁ ተገልጿል። 

5. በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፌስቡክና ኢንስታግራም ያጋራነውን መልዕክት ያላግባብ አንስተውብናል ወይም ሪፖርት አድርግን አላነሱትም ያሉ 1.1 ሚሊዮን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ተገልጋዮች ይግባኝ መጠየቃቸውን ሜታ ያቋቋመው የበላይ ተመልካች ቦርድ (Oversight Board) አስታውቋል። ቦርዱ እ.አ.አ ከጥቅምት 2020 እስከ ታህሳስ 2021 ዓ.ም ባሉት ጊዚያት ተቀበልኳቸው ካላቸው ይግባኞች ውስጥ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካውያን ድርሻ  1.7% ብቻ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል። 

6. በ280 ሆህያት የተገደብ መልዕክት ብቻ ማጋራትን የሚፈቅደው ትዊተር ረዘም ያለ ጽሁፍ መጻፍ ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች  ‘ኖትስ’ (Notes) የተሰኘ አገልግሎት መጀመሩን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል። አዲሱ አገልግሎት በትዊተር ረዘም ያለ ጽሁፍ ማጋራት የሚፈልጉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ተጠቃሚዎች ረዘም ያለ ይዘት ማጋራት እንዲችሉ ያደርጋል። በተጨማሪም ከጽሁፉ ጋር ቪዲዮ፣ ፎቶ፣ ጃአይኤፍ (GIF) ማያያዝ የሚያስችል ሲሆን ከተጋራ በኃላ አርትዖ እንደሚፈቅድ ተገልጿል። 

7. ፌስቡክ ላይ መረጃ ለማሰስና ለመቃኘት (monitoring) በባለሙያዎች ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ክራውድታንግል (CrowdTangle) የተሰኘውን መገልገያ ሜታ በቅርቡ ከአገልግሎት ለማስወጣት መወሰኑን ብሉምበርግ በሳምንቱ መጨረሻ ዘግቧል።። ክራውድ ታንግል በተለይም ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በተደራጀ መልክ ለማሰስና ለመቃኘት መረጃ አጣሪዎች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ተመራማሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ ያውሉት ነበር። ሜታ መገልገያውን ለምን ከአገልግሎት እንደሚያስወጣው ማብራሪያ አልሰጠም።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::