ምስሎችን ለማጣራት እና ትዊተርን ለሚድያ አገልግሎት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ነፃ መተግበሪያዎች!

መረጃዎችን እንዲሁም ምስሎችን ለማጣራት የሚረዱ የተለያዩ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች ይገኛሉ። ከድረ- ገጾች እስከ ሞባይል መተግበሪያዎች ድረስ አይነታቸው ብዙ የሆኑ የመረጃ ማጣራትን ስራ የሚያቀሉ እና እውነተኝነታቸውን የሚያረጋግጡ መሳሪያዎች አሉ። ከእነሱም መካከል: 

1.  ቲንአይ(TinEye): ይህ መተግበሪያ ምስሎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ለማጣራት የሚጠቅመን ድረ-ገጽ ነው። የምንፈልገው ምስል ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ውሎ ከነበረ መቼ እና የት እንዲሁም በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደዋለ ያሳውቀናል። በዚህ መተግበርያ በፎቶሾፕ የተነካኩ ምስሎችንም ፈልጎ ማግኘት ይቻላል። ድረ-ገፁ www.tineye.com ሲሆን አጠቃቀሙ ደግሞ ድረ-ገጹ ላይ የምንፈልገውን ምስል ከኮምፒተር ወይም ከስልካችን ላይ መርጠን በማስገባት መፈለግ ነው። ያስገባነውን ምስል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ቲንአይ ከኢንተርኔ ላይ ከወሰዳቸው 45 ቢሊዮን ምስሎች ውስጥ ይፈለግለናል። ምስሉን እና ምስሉን የሚመስሉ በርካታ ውጤቶችን ያወጣል፣ ከወጡት ምስሎች ውስጥም የምንፈልገውን መርጠን ስንመለከት ከዚህ በፊት ይህ ምስል የት ጥቅም ላይ እንደዋለ ማየት እንችላለን። ምንም ውጤት ካልመጣ ደግሞ ምስሉ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ አልዋለም ማለት ነው፣ ወይም ምስሉ የቲንአይ ክምችት ውስጥ የለም ማለት ነው። ይህን መሳሪያ በነጻ መጠቀም መቻሉ አንዱ ጥሩ ጎኑ ነው። 

2.  ፎቶ ፎሬንዚክስ(Photo Forensics): ይህ መተግበርያ የሚጠቅመን የአንድን ፎቶ በፎቶሾፕም ሆነ በሌላ መተግበሪያ አለመነካካቱን እና ከዋናው ፎቶ አለመቀየሩን ነው። አጠቃቀሙ ደግሞ ወደ www.fotoforensics.com ከገባን በሁዋላ በመጀመሪያው ገጽ ማረጋገጥ የምንፈለገውን ፎቶ የምናስገባበት ገጽ እናገኛለን። የምንፈልገውን ፎቶ ከኮምፒተራችን ወይም ከስልካችን መርጠን ካስገባን በሗላ ፈልጎ ሲጨርስ ፎቶው ተነካክቶ ከሆነ ምኑ ጋር እንደተነካካ ወይም እንደተቀየረ የሚያሳየን ፎቶ ይመጣል። ያስገባነው ፎቶ ላይ ወጥ የሆነ ቀለም ብቻ የምናይ ከሆነ ፎቶ እውነተኛ ፎቶ መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን፣ አለበለዚያ ደሞ አንድ ቦታ ላይ በብዛት ለየት ያለ ቀለም ወይም ነጣ ያለ ቀለም አንድ ቦታ ላይ ተከማችቶ ካገኘን ያ ፎቶ መነካካቱን መረጋገጥ እንችላለን። ፎቶውም ከየት እንደመጣ(ከካሜራ ወይስ ከፎቶ ሾፕ) ማየት እንችላለን። 

3. ትዊትዴክ (TweetDeck): ይህ መተግበርያ ደግሞ ትዊተርን በተሻለ መልኩ ለመጠቀም ይረዳል። የተለያዩ ገጾችን (እንደ ሜሴጆች፣ የትዊተር የፊ ገጽ፣ የተለያዩ የትዊተር ገጾችን እና የመሳሰሉትን) በአንድ ገጽ ላይ ለማየት ያስችለናል። ትዊት ማድረግ የምንፈልጋቸውን ፅሁፎችንም አስቀድመን ጽፈን በሌላ ቀን ወይም ሰዓት ላይ በራሱ ፖስት እንዲያደርግ ማድረግ እንችላለን።

አጠቃቀሙ www.tweetdeck.com ላይ ከገባን በሗላ ወደ ትዊተር አካውንታችን የሚያስገባንን ስማችንን እና የይለፍ ቃላችንን አስገብተን መቀጠል ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::