ከሰዐታት በፊት ጀምሮ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ድረ-ገጽና የቴሌግራም ቻናል ሃክ ስለመደረጋቸው የሚገልጹ መልዕክቶችን ተመልክተናል!

ድረ-ገጹና የቴሌግራም ቻናሉ ‘MarbeyliWerom & RootAyyıldız’ በተባሉ ሀከሮች (ፈልቃቂዎች) መጠቃቱ የተገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያ ቼክ የፈልቃቂዎቹን ማንነት ለማወቅ የድረ-ገጽ ዳሰሳ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ቼክ ባገኘነው መረጃ መሰረት ‘RootAyyıldız’ እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም በቱርክ አንካራ የተመሰረተ የፈልቃቂዎች ቡድን ሲሆን በተለይ መንግስታዊ የሆኑ ድረ-ገጾችን በማጥቃት በመላው አለም ይታወቃል።
ይህ ቡድን ራሱን እንደ አርበኛ የሚቆጥር ሲሆን ለቱርክ ሪፐብሊክ ዘብ ስለመቆሙ ይገልጻል። ቡድኑ ከዚህ ቀደም የአሁኑን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን የምርጫ ዘመቻ ድረ-ገጽ፣ የግሪክን የውጭ ጉዳይና የሀገር ውስጥ ሚኒስቴሮችን፣ በርካታ የህንድ የትምህርት ተቋማትን፣ የአውሮፓ ምክር ቤት እና ሌሎችን ድረ-ገጾች አጥቅቷል። ‘MarbeyliWerom’ በተመሳሳይ መቀመጫውን ቱርክ ያደረገ የሀከሮች ቡድን ነው።
ኢትዮጵያ ቼክ ማምሻውን ከፋና ብሮድካስቲንግ ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ቡድኖቹ ጥቃቱን ያደረሱት በአንድ የፋና ባልደረባ አካውንት አማካኝነት ሲሆን አሁን ላይ ድረ-ገፁን እና የቴሌግራም ቻናሉን በከፊል ለመመለስ ተችሏል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::