ብዙዎችን ያሳሳተው የኢሎን መስክ ከትዊተር የመታገድ ዜና

ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ሰሞኑን በስፋት መነጋገሪያ የሆነ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጫፍ የደረሱ ይመስላል። “የንግድ ማግኔት” የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው እኝህ ባለሃብት በቅርቡ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት የገቡትን ስምምነት ለማፍረስ ፍላጎት እንዳላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት ለትዊተር ሃላፊዎች የገለጹት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ነበር።

ለዚህ ውሳኔ ያደረሰኝ ብለው እንደምክንያት ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል ትዊተር በፕላትፎርሙ ላይ አሉ ብሎ የገለጸላቸውን የሀሰተኛ አካውንቶች ቁጥር ማረጋገጥ አለመቻላቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

“በፕላትፎርሙ ላይ ያሉትን ሀሰተኛ አካውንቶችን በተመለከተ ትዊተር ለኢሎን መስክ ያቀረባቸው መረጃዎች የውሸት እና አሳሳች ናቸው” በማለት ባለሃብቱ ለትዊተር በላኩት ደብዳቤ ይከሳሉ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎችም ይህ ልዩነት ተካሮ ወደ ክስ ሊያመራ እንደሚችል በመተንበይ ላይ ናቸው።

ይህንን ተከትሎም አንድ የትዊተር ተጠቃሚ ‘ኢሎን መስክ ትዊተርን አልገዛም ስላለ ከትዊተር ታገደ’ ከሚል ዜና ጋር መታገዱን የሚያሳይ አንድ የስክሪን ቅጂ አያይዞ ትዊት ያደርጋል። ይህ ይዘት ከ24 ሺህ ጊዜ በላይ ሪትዊቶችን፣ ከ136 ሺህ ጊዜ በላይ የመውደድ (Like) ግብረመልሶችን እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስተናግዷል።

ነገር ግን ኢሎን መስክ ከትዊተር ታግዷል የሚለው መረጃ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች ለመሆኑ ፍንጭ የሚሰጥ አንድ ምልክት ነበረው። ይህንን ያጋራው ተጠቃሚ በገጹ ላይ የሚለጥፋቸው ይዘቶች ፋይናንስ ነክ ቀልድና ስላቅ (meme and satire) እንደሆኑ ስለ ገጹ ምንነት የገለጸበት ክፍል ላይ አስፍሯል። ይህንን ያስተዋለ ማንኛውም ሰው የባለሃብቱን ሙሉ ስም ተጠቅሞ ትዊተር ላይ ቢፈልግ፣ የተረጋገጠው (Verified) የኢሎን መስክ አካውንት አለመታገዱን ማግኘት ይችላል። ያለብዙ ድካምም ‘ኢሎን መስክ ታግዷል’ የሚለው መረጃ ውሸት መሆኑን ይደርስበታል።

ታዲያ ይህ መረጃ በዚህ ልክ እንዴት ሊያሳስት ቻለ?

ብዙ ሰዎች በዚህ መረጃ የተሳሳቱበት ዋናው ምክንያት የሁለቱም አካውንት መጠቀሚያ ስማቸው (ወይም twitter handle) መመሳሰል ነው። ከላይ ሲታይ ሁለቱም አካውንቶች ላይ የሚታየው ስም @elonmusk የሚል ነው። ነገር ግን ሀሰተኛው አካውንት በ “l” (ኤል) ምትክ የተጠቀመው capital ‘i’ (አይ) የሚለውን ፊደል ነው።

ትዊተር የሚጠቀምበት Sans Serif የሚባለው የፊደል አይነትም በሁለቱ ፊደላት መካከል ያለውን ልዩነት በቀላሉ መለየት ስለማያስችል፣ ሰዎች በዚህ ለቀልድ ተብሎ በተነገረ ሀሰተኛ መረጃ ሊሳሳቱ ችለዋል።

መረጃው በተለቀቀበት ጊዜ የነበረውና የአብዛኞችን ትኩረት ስቦ የሰነበተው ዜናም ይህ አሳሳች ይዘት በስፋት ለመሰራጨቱ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታመናል።

ኢትዮጵያ ቼክም ብዙዎችን ካሳሳተው ከዚህ ክስተት ልንማር የምንችለው ነገር አለ በሚል እምነት ይህንን ጽሁፍ አቅርቦላችኋል። መረጃዎችን ከማጋራትችን በፊት አስፈላጊ የሆኑ የጥቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::