“እጅግ ያሳፍራል። በሶሻል ሚድያ ብዙ ጥሩ ጥሩ ስራዎች ይሰራሉ፣ እንዲህ በሰው ህይወት መቀለድ ግን አሳዛኝ ነው”— አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ለኢትዮጵያ ቼክ

ታዋቂው እና አንጋፋው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች በቴሌግራም፣ ፌስቡክ እና ትዊተር አማካኝነት ትናንት እና ዛሬ ሲሰራጩ ተመልክተናል። ከነዚህም መሀል አርቲስቱ ህይወታቸው እንዳለፈ ተደጋግሞ ተፅፏል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ አርቲስት ሙላቱን ያናገረ ሲሆን በዚህ ድርጊት ማዘናቸውን ገልፀዋል።

“ህልማቸዉ፣ ፍላጎታቸዉ ይሄ ነዉ አልሆነም እንጂ። በጣም የሚያሳዝን ነገር ነዉ። የዉሸት ወሬ ነዉ፣ እኔ ደህና ነኝ። ያሳዝናል! ብዙ ስራዎች አሉኝ ስለነሱ ቢያወሩ አከብራቸዉ ነበር” ያሉት አርቲስት ሙላቱ በጀርመን፣ ስፔን እና ሌሎች ሀገራት ስራዎችን አቅርበው አሁን መመለሳቸውን ለኢትዮጵያ ቼክ አሳውቀዋል።

አክለውም “በሶሻል ሚድያ ብዙ ጥሩ ጥሩ ስራዎች ይሰራሉ፣ እንዲህ በሰው ህይወት መቀለድ ግን አሳዛኝ ነው። እኔ አሁን ላይ የተለያዩ የጥናት ፅሁፎችን እያዘጋጀሁ እና በቅርቡ ስራዎቼን በዴንማርክ፣ ስዊድን እና አሜሪካ ለማቅረብ እየሰራሁ ነው” ብለዋል።

አርቲስቱ እንዲህ አይነት የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው ሶሻል ሚድያን ለበጎ እንዲጠቀሙበት መክረዋል።

ኢትዮጵያ ቼክም መረጃዎችን በቀጥታ ተቀብለን ከማሰራጨታችን በፊት እውነተኝነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባን ሊገልፅ ይወዳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::