የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት!

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔ በስኮትላድ ግላስኮ ከተማ ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው ቅዳሜ ስምምነቶችን በማሳለፍ ተጠናቋል። ዋነኛው አጀንዳውን ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ብክለት መቀነስና ታዳጊ አገሮች የአየር ንብረት ቀውስን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት በገንዘብ መደገፍ ላይ ያደረገው ይህ ጉባዔ ከ200 በላይ ሀገሮች ተሳትፈውበታል። ኢትዮጵያም በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕ/ር ፍቃዱ በየነ በተመራ ቡድን የተወከለች ሲሆን በመጭዎቹ ዓመታት አሳካዋለሁ ያለችውን ግብ አቅርባለች።

የጉባዔው ዋና ትኩረት ከነበሩ አጀንዳዎች ባልተናነሰ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች (conspiracy theories) በስፋት የተሰራጩባቸው ሳምንታት የነበሩ ሲሆን ይህን ተግዳሮት መቋቋም በሚቻልበት አግባብ ላይ ያተኮሩ የጎንዮሽ ውይይቶች፣ የሚዲያ ፓነሎች፣ የምርምርና የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ጽሁፎች (media litracy) በድረ-ገጾች በርከት ብለው ሲቀርቡ አስተውለናል።

የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች ላይ አትኩረው የሚሰሩ ምሁራንና አክቲቪስቶች እንደሚሉት የተግዳሮቱ የጀርባ አንቀሳቃሾች የተለያየ ፍላጎት ያላቸው መልከ ብዙ ተዋንያን ናቸው። ግዙፍ የነዳች አምራች ድርጅቶች የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች የሚያሰራጩ ቡድኖችን በቀዳሚነት በገንዘብ ስለመደገፋቸው በመረጃ የተደገፈ ክስ የሚቀርብባቸው ሲሆን ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞችና ቡድኖች እንዲሁም በተቃርኖ የቆሙ ሳይንቲስቶች (contrarian scientists) ከተወቃሾች መካከል ይገኙበታል።

እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩትዩብ የመሳሰሉ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረክ ሰጪ ድርጅቶች የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች መረን በለቀቀ ሁኔታ እንዲሰራጩ በር ከፍተዋል ተብለው በስፋት በመወቀስ ላይ ሲሆን አልጎሪዝማቸውን ዘመምተኛነት (algorithmic bias) ማረቅ አለመቻላቸው የወቀሳው ዋና ትኩረት ሲሆን ተመልክተናል።

የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከቱ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች ላይ አትኩረው የሚሰሩ ምሁራንና አክቲቪስቶች እንደሚሉት ተዋኞቹ ሶስት ዋና ዋና ግቦች አሏቸው። ግቦችም የአየር ንብረት ለውጥ እውነታን በተመለከተ ጥርጣሬ መጫር፣ የአየር ንብረት ለውጥ አጣዳፊነትን በተመለከተ መካድና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ አትኩረው የሚሰሩ ተመራማሪዎችንና የምርምር ውጤታቸው ላይ እምነት እንዳይኖር ማድረግ ናቸው። ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ብዥታን የሚፈጥር ሲሆን ፖለቲካዊ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዳይወሰዱ ያደናቅፋል።

ይህን ተግዳሮት ለመግታትም የአየር ንብረት ለውጥንና እውነታውን በትምህርት ካሪኩለም ማካተት፣ እውነተኛ መረጃን ለህብረተሰቡ በየጊዜው ማቅረብ እንዲሁም የሚዲያ አጠቃቀም ንቃትን ማሳዳግ በመፍትሄነት ይቀርባሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::