በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስም እየተሰራጩ ከሚገኙ ሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች እንጠንቀቅ!

የኮ/ር አትሌት ደራርቱ ቱሉን ስም እና ምስል በመጠቀም የተከፈቱ በርካታ የፌስቡክ አካዉንቶችና ገጾች ሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎችን እያጋሩ እንደሆነ ተመልክተናል።

እነዚህ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስም የተከፈቱ አካዉንቶችና ገጾች በመቶዎች አለፍ ሲልም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸዉ ናቸዉ።

አንዳንዶቹ ገጾች በተለይ 18ኛዉ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ ኦሬገን በተካሄደበት ወቅት ፕሬዝዳንቷ የጻፉት በማስመሰል የተለያዩ ጽሁፎችን ሲያጋሩ ቆይተዋል።

በአሁን ሰዓትም የፕሬዝዳንቷን ስም እና ምስል በመጠቀም የተከፈቱ ገጾችና አካውንቶች ፖለቲካዊና ሌሎች ጉዳዮችን የያዙ ጽሁፎች (ጥላቻ ነክ ጽሁፎችን ጨምሮ) እያጋሩ ይገኛሉ።

ለምሳሌ ያህል ይህ በምስሉ ላይ የሚታየው ከ21 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሀሰተኛ ገጽ 24 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ 17 በጽሁፍ እና ምስል የታገዙ የተለያዩ መረጃዎችን አጋርቷል። በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም ጽሁፎቹን አጋርተዋል፣ ሀሳብና አስተያየታቸዉንም ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አንድ የፌስቡክ አካዉንት ብቻ እንዳላትና በእርሷ ስም የተከፈቱ ሌሎች አካዉንቶችና ገጾች የእርሷ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጣለች።

ትክክለኛው፣ ነገር ግን ብዙ መረጃዎች የማይቀርብበት የኮ/ር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የፌስቡክ አካዉንት ይህ እንደሆነ አረጋግጠናል።

ሀሰተኛና ተመሳስለዉ የተከፈቱ አካዉንቶችና ገጾች ለሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ትከከለኛ አካዉንቶችን ብቻ እንከተል። የአካዉንቱ ወይም ገጹ ትክክለኛነት አጠራጣሪ ከሆነም መረጃዎችን ከማጋራታችን በፊት ቆም ብለን እናስብ፤ ስለ አካዉንቱ/ገጹ ትክክለኛነትም እናረጋግጥ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::