ተመሳስለው የተከፈቱ አካውንቶች፣ ገፆች እና ቻናሎች ጉዳይ!

በማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ላይ አስመስለው የተከፈቱ አካውንቶች፣ ገፆች እና ቻናሎች በብዛት እየታዩ ይገኛሉ፣ ለተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲውሉም ይስተዋላሉ።

እነዚህም የፖለቲካ ሰዎችን ለመደገፍ ወይም ለመንቀፍ፣ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ለማካፈል (agenda setting)፣ መከፋፈልን እና አለመተማመንን ለመፍጠር፣ ታዋቂ ሰዎችን በማስመሰል በስማቸው ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማስተላለፍ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

በዚህ ወር ብቻ በኢትዮጵያ ቼክ የተጋለጡ የሀሰተኛ አካውንቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል:

1. በአቶ ለማ መገርሳ ስም የተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶች እና ገፆች: የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት በአቶ ለማ መገርሳ ስም እና ምስል የተከፈቱ በርካታ የፌስቡክ አካውንቶች አሉ። ኢትዮጵያ ቼክ ለማረጋገጥ እንደቻለው አቶ ለማ የፌስቡክ አካውንትም ሆነ ገፅ የላቸውም።

2. የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ ናቸው የተባሉ እና “ጆርጅ ቦልተን” በሚል ስም የተከፈተ የትዊተር አካውንት እንዳለም ጠቁመን ነበር። ይህ አካውንት በበርካታ ሰዎች እና ገጾች ላይ ሲዘዋወር የነበረው ሲሆን ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት የፕሮፋይል ምስሉ (profile picture) የረቀቀ የማስመሰል ጥበብን (deep fake) በመጠቀም የተሰራ ሀሰተኛ ፎቶ መሆኑንን አረጋግጧል።

3. በኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ በአቶ ታዬ ደንደአ የተከፈተ የትዊተር አካውንት እንዲሁ እንደሚገኝ ጠቁመናል። የአቶ ታዬ ትክክለኛ የትዊተር አካውንት ከ2,440 በላይ ተከታዮች ያለው ነው።

4. በጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናል ጀኔራል አበባው ታደሰ ስም እና ምስል የተከፈተ የፌስቡክ ገጽ እንዲሁ በርካታ መረጃዎችን እያጋራ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቼክ የገጹን ሀሰተኛነት ካጋለጠ በኃላ ስሙ ወደ ‘Ethiopia Today’ ቀይሮ ቆይቷል። ከጥቂት ቀናት በፊት የገጹ ስም እንደገና ወደ ‘ሌ/ጀ አበባው ታደሰ’ መቀየሩን አስተውለናል። ገጹ የሌተናል ጀኔራል አበባው ታደሰ አለመሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

5. በጋዜጠኛ ቤተልሄም ታፈሰ ስም እና ምስል የተከፈተ የፌስቡክ ገፅ ይገኛል። የጋዜጠኛዋን ስም እና ምስል በመጠቀም የተከፈተ የፌስቡክ ገጽ የእርሷ አለመሆኑን ጋዜጠኛ ቤተልሔም ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጣለች።

ሀሰተኛ እና ተመሳስለው የተከፈቱ አካውንቶችን እንዴት መለየት ይቻላል?

1.  የአካውንቱን ወይም ገፁን የፕሮፋይል ምስል በአፅንኦት መመልከት እና አጠራጣሪ ከሆነ ማጣራት ማድረግ

2. የአካውንቱን ስም መመልከት እና አጠራጣሪ እንዲሁም ቁጥሮች ወይም ኢሜይል አድራሻ ብቻ ያለው ከሆነ ማጣራት ማድረግ

3. አጭር የማንነት መግለጫ (profile bio) ማየት፣ አብሮ የቀረበ ሊንክ ካለ ከፍቶ መመልከት

4. የተከታዮች ብዛት እና አካውንቱ የተከፈተበት ግዜ ትክክለኛነትን ባይገልፅም እርሱንም በደንብ ማጤን።

5. የሚቀርቡ ርዕሶች እና ጉዳዮችን መመልከት፣ ሁል ግዜ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው እና የሌሎች ሰዎችን ስራዎች የሚያቀርብ ከሆነ በመጠራጠር ማጣራት ማድረግ

6. ከሌሎች አካውንቶች ጋር ያለውን መስተጋብር ማየት፣

ስለሆነም ተመሳስለው የተከፈቱ የሀሰተኛ ገጾች እና አካውንቶችን ለይቶ በማወቅ እና ባለመከተል ከሀሰተኛና ከተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ራስዎን ይጠብቁ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::