ፌስቡክ ከሰሞኑ ይቀይረዋል የተባለው ዋና የካምፓኒውን ስም ሲሆን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጠው የፌስቡክ መተግበሪያ (App) ስያሜውን ይዞ የሚቀጥል ይሆናል! 

ፌስቡክ የስም ለውጥ ሊያደርግ ማቀዱን የተመለከቱ መረጃዎች ዛሬ በስፋት ተሰራጭተዋል። ዜናውን በመጀመሪያ ይዞት የወጣው ከቴክኖሎጅ ጋር የተገናኙ መረጃዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ዘ-ቨርጅ (The Verege) የተባለ ድረ-ገጽ ሲሆን ፌስቡክ በሚቀጥለው ሳምንት የስያሜ ለውጥ ሊያደርግ ማቀዱን ስለጉዳዩ ቀጥተኛ እውቀት ካላቸው ምንጮች መስማቱን አስነብቧል። 

እንደ ድረ-ገጹ ዘገባ ፌስቡክ የሚቀይረው ዋና የካምፓኒውን ስም ሲሆን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጠው የፌስቡክ መተግበሪያ ስያሜውን ይዞ የሚቀጥል ይሆናል። ‘Facebook, Inc.’ በመባል የሚጠራው ካምፓኒ በስሩ ከፌስቡክ በተጨማሪ ዋትስ አፕ፣ ኢንስታግራም፣ ኦክሎስ እና ሌሎችን የሚያስተዳድር መሆኑ ይታወቃል። 

የስም ለውጡ ፌስቡክ ከማህበራዊ ሚዲያ መድረክነት ባሻገር የመሆን መሻቱን ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ዘ-ቨርጅ ዘግቧል። በማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭነቱ የሚታወቀው ፌስቡክ ካምፓኒ በቅርቡ የባለሶስት አውታር እና ከዛም የሚሻገሩ ግንኙነት ሰጭ ምርቶች ላይ አጽንዖት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የአውግመንትድ ሪያሊቲ መነጽሮችን (AR Glasses) እንደ እጅ ስልኮች በስፋት ተደራሽ ለማድረግ መወጠኑም በተደጋጋሚ ተገልጿል። 

በተጨማሪም አዲሱ ስያሜ ከአገልግሎቱ ጋር ተያይዞ በሚነሱ ትችቶች የጎደፈ ስሙንም ለማደስ ያቀደ መሆኑን ድረ-ገጹ አስነብቧል። ፌስቡክ የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት የሚጠበቀውን ያክል ጥረት አላደረገም ተብሎ የሚተች ሲሆን በቅርቡ ከካምፓኒው በመልቀቅ አውቀዋለሁ ያለችውን የፌስቡክ ሚስጢር ለሚዲያዎችና ለአሜሪካ ኮንግረስ ይፋ ያደረገችው ፍራንሲስ ኅገን ፌስቡክ ከደንበኞቹ ደህንነት ይልቅ ትርፍን ያስቀድማል ስትል መደመጧ ይታወሳል። ፍራንሲስ ኅገን የፌስቡክን ድክመት ለመግለጽም በኢትዮጵያና በማይናማር ተከሰቱ ያለቻቸውን የፖለቲካ ምስቅልቅሎች በምሳሌነት አቅርባ ነበር። 

ግዙፍ የሆኑ ካምፓኒዎች የስያሜ ለውጥ ማድረጋቸው የተለመደ ሲሆን ጎግል እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም ስሙን ወደ አልፋቤት (Alphabet) መቀየሩ ይታወቃል። በስሩም የኢንተርኔት ማሰሻ አገልግሎት የሚሰጠውን ጎግልን ጨምሮ በርካታ መተግበሪያዎችንና አምራች ድርጅቶችን ያስተዳድራል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::