ፌስቡክ: ከማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭነት ወደ እውነታ ከሳች (Metaverse) ቴክኖሎጂዎች መሸጋገር!

ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ካምፓኒ ፌስቡክ ስሙን ወደ ሜታ (Meta) መቀየሩን ትናንት ምሽት ይፋ አድርጓል። ኮኔክት በመባል በሚታወቀው የካምፓኒው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ይፋ የተደረገው አዲሱ ስያሜ ፌስቡክ ከማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭነት ወደ እውነታ ከሳች (Metaverse) ቴክኖሎጂዎች የመሸጋገር መሻቱን ይገልጻል ተብሏል።

የድርጅቱ መስራች ማርክ ዙከርበርግ የስም ቅያሬውን በተመለከተ ባጋራው ረዘም ያለ ጽሁፍ አዲሱ የካምፓኒው ስም “ባሻገር” (beyond) የሚል ትርጉም ካለው የግሪክ ቃል “ሜታ” (meta) መውሰዱን የገለጸ ሲሆን ድርጅቱ ከአሁን በሗላ እውነታ ከሳች የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማበልጸግ ቀዳሚ ትኩረቱ እንደሚሆን አብራርቷል።

ፌስቡክ የትኩረት ማዕከሌ ይሆናለው ያለው ሜታቨርስ የባለሶስት አውታር (3D) እና ከዛ ባሻገር ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በማሳለጥ እውነታ እንደሚከስት የተገለጸ ሲሆን በቦታና በጊዜ የተራራቁ ሰዎች አብረው ያሉ ያህል እንዲሰማቸው በማስቻል ማህበራዊ ትስስርን ወደ አንድ እርከን ከፍ ያደርጋል ተብሏል። ይህንም በቦታ የተራራቁ ሰዎች አብረው ያሉ ያህል ተሰምቷቸው ወደ ስራ ቦታ ሳይሄዱ ስራ አብረው እንዲሰሩ፣ በአካል ሳይገናኙ እንደተገናኙ ሆነው እንዲጫወቱ፣ ማህበራዊ ትስስራቸውን እንዲያሳልጡ ወዘተ ያስችላቸዋል።

ካምፓኒው የሜታቨርስ ቴክኖሎጂን እውን ለማድረግ በመጭዎቹ አመታት በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ኢንቨስት እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ሜታቨርስ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ቀጣይ ምዕራፍ እንደሚሆን እናምናለን ሲል ዙከርበር በጽሁፉ አስነብቧል።

ፌስቡክ ዋና የካፓኒውን ስም ወደ ሜታ ይቀይር እንጂ በስፋት የሚታወቅባቸው ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራምና ሌሎች መተግበሪያዎች ስያሜያቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ይሆናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::