ለመራጭነት በተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ላይ የተነሱ ጥያቄዎች እና የተሰጡ ማብራሪያዎች! 

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜዊ የመራጮች ምዝገባ መረጃን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በርከት ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በተለይም በአፋር እና በሱማሌ ክልሎች ለመራጭነት የተመዘገቡ ዜጎች ቁጥር ላይ ግሽበት መመልከታቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል። አንዳንዶቹ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የስነ-ህዝብ ትንበያን እንደማመሳከሪያ አቅርበዋል። 

በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት የተዘዋወረ አንድ ሰንጠረዥም ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የስነ-ህዝብ ትንበያ አኳያ 50%ቱ ለመራጭነት ብቁ ቢሆን በሱማሌ ክልል 127%፣ በአፋር ክልል 180% እንዲሁም በጋምቤላ ክልል 118% መራጮች እንደተመዘገቡ ያሳያል። (ይህ በስፋት የተሰራጨ ሰንጠረዥ የየትኛውን ዓመት የስነ-ህዝብ ትንበያ እንደተጠቀመ አልተገለጸም)። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ‘በአንዳንድ ክልሎች የመራጮች ቁጥር ላይ ግሽበት ታይቷል፤ ምክንያቱ ምን ይሆን?’ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን ሠብሳቢዋ የመራጮችን ቁጥር ለመተንበይ ከ13 ዓመታት በፊት የተደረገ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት ተግባር ላይ በመዋሉን ጠቅሰዋል። 

የመራጮችን ቁጥር በተመለከተ ቦርዱ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ትንበያን እንደሚጠቀሙ የገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን “ስታስቲክስ ኤጀንሲ ፕሮጀክሽኑን (ትንበያውን) እየሰራ ያለው የዛሬ 13 ዓመት አድርጌዋለሁ በሚለው ቆጠራ ላይ ተመስርቶ ነው፤ በዛ ላይ ተመስርቶ የሚሰጠው ፕሮጀክሽን የታማኝነት መጠኑ አነስተኛ ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ ዛሬ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚጠቁመው ቦርዱ ከ2007ቱ ሀገራዊ ምርጫ ያገኘውን የመራጮች ቁጥርን የያዘ የመረጃ ቋት ለምዘና እንደሚገለገልበትም ጠቅሷል። 

የመራጮች ቁጥር ላይ ግሽበት ታይቶባቸዋል ተብለው በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከተጠቀሱት አንዱ የሱማሌ ክልል ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ዑመር በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጻቸው ምላሽ ይሆናሉ ያሏቸውን ምክንያቶች አስፍረዋል። 

እንደ አቶ ሙስጠፌ ማብራሪያ ባለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት ከሀገር ውስጥ ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የገቡ 600,000 ዜጎች እንዲሁም ባለፉት ሶስት ዓመታት በጎረቤት ሀገራት በስደተኝነት የቆዩ 700,000 የክልሉ ተወላጆች መመለሳቸው ለቁጥሩ መጨመር በምክንያትነት አቅርበዋል። በተጨማሪም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በተደረገበት ወቅት በክልሉ የነበረውን አለመረጋጋት እንዲሁም በአንዳንድ ኪስ ቦታዎች ቆጠራ አለመደረጉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያ ቼክ በኢትዮጵያ ብቁ የሆኑ መራጮችን ቁጥር ለማወቅ የስታስቲክስ ኤጀንሲ ድረገጽን የተመለከተ ሲሆን በድረገጹ የቀረቡ ትንበያዎች ዕድሜን ስላላካተተ ትክክለኛውን ቁጥር ማወቅ አልቻለም።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::