“የሚፈለገዉን የትምህርት ደረጃ ብናሟላም የዉስጥ እድገት ዉድድሮችን መወዳደር ተከልክለናል” ያሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ሰራተኞች ጉዳይ!

የዉስጥ እድገት ዉድድር ማስታወቂያ በሚወጣበት ጊዜ የሚፈለገዉን የትምህርት ደረጃ ቢያሟሉም መወዳደር መከልከላቸዉንና ጉዳዩንም እንድናጣራ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ሰራተኞች ጥቆማ ደርሶናል።  

ሰራተኞቹ ጉዳዩን በተመለከተ ለተቋሙ የበላይ አመራሮች ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም “ትንሽ ጠብቁ” ከሚል ዉጭ መፍትሄ ያለማግኘታቸዉንም ይናገራሉ።    

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂና የት/ት ማስረጃዉ እያላቸዉ ከዛ በታች በሆነ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩና በቅጥር ወቅትም የመጀመሪያ ዲግሪ የት/ት ማስረጃቸዉን ያላስያዙ (ያላስመዘገቡ) ናቸው። 

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ቅሬታ አቅራቢ የተቋሙ ሰራተኛ “በኛ ፊልድ የዉስጥ ማስታወቂያ ያወጡና ቴምፖ ይዘን ስንሄድ ‘የናንተ ከቅጥር በፊት የነበረ ነዉ፤ ዉስጥ ሆናቹ አይደለም ያሻሻላችሁት። ደብቃችሁ ስለገባችሁ ተቀባይነት አይኖረዉም’ ነዉ የሚሉን” ሲል ለኢትዮጵያ ቼክ ነግሯል። 

በዚህም ምክንያት እሱ በተመረቀበት የሙያ ዘርፍ በርካታ የውስጥ እድገት ማስታወቂያዎች ቢወጡም ተወዳድሮ የስራዉን ደረጃ ማሻሻል እንዳልቻለ ይናገራል። 

ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የሰው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ የሆኑትን አቶ አታላይ አበበን አናግሯል። 

እርሳቸዉም ሰራተኞቹ ያነሱትን ቅሬታ እንደሚያዉቁት ነገር ግን የዉስጥ እድገት ዉድድርን መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበርና ተቋሙ የፈረሙት የህብረት ስምምነትን መሰረትን አድርገዉ እያከናወኑ እንደሚገኙ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል። 

“የተቋሙ የህብረት ስምምነት አለ፤ የሰራተኛ አዋጅን መሰረት ያደረገ። ከሱ በመነሳት የተዘጋጀ የህብረት ስምምነት አለ። መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበርና ተቋሙ የፈረሙት ማለት ነዉ” በማለትም ይህ የተቋሙ የዉስጥ አሰራር ደንብ መሆኑን ይናገራሉ። 

“እዛ ላይ (የህብረት ስምምነቱ ላይ) በግልጽ የተቀመጠዉ ምንድነዉ? ከዉጭ ሰዎች ሲቀጠሩ ቀድመዉ ይዘዉት የሚመጡት ዲግሪ ካለ እሱ መጀመሪያ ካልተመዘገበ በኋላ ታሳቢ አይደረግም” ብለዋል አቶ አታላይ አበበ። 

ነገር ግን እነዚህ ሰራተኞች የዉጭ የስራ ቅጥር ማስታወቂያ በሚወጣበት ጊዜ ተቋሙ የሚጠይቀዉን የመመረቂያ ነጥብ የሚያሟሉ ከሆነ ከዉጭ ተወዳዳሪዎች ጋር መወዳደር የሚችሉ መሆኑን ነግረዉናል። 

“ዝቅ ብለዉ መስራታቸዉን እናደንቃለን። ዉድድሩን አንነፍጋቸዉም። ነገር ግን የሚፈለገዉን ነጥብ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::