ትዊተር ኩባንያ ትዊቶችን የማረምያ (ኤዲቲንግ) አገልግሎት ለመጀመር እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል!

የድርጅቱ የኮሚኒኬሽን ቡድን ዛሬ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው አጭር መልዕክት የትዊተር ተጠቃሚዎች ያጋሯቸውን መልዕክቶች ማረም (ኤዲት ማድረግ) እንዲችሉ የሚረዳው አገልግሎት ከወራት በኋላ ወደ ሙከራ እንደሚገባ አስታውቋል።

የኤዲቲንግ አገልግሎትን በተመለከተ በርካቶች ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ያስታወሰው የኮሚኒኬሽን ቡድኑ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ኤዲቲንግን የተመለከቱ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጿል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ አንድ የድርጅቱ ሃላፊ የሆኑት ጄይ ሱሊቫን ጉዳዩን በተመለከተ በትዊተር ገጻቸው ተጨማሪ ማብራሪያዎችን አስነብበዋል። ሃላፊው የኤዲቲንግ አገልግሎቱ ስህተቶችንና የሆህያት ዝንፈቶችን እንዲሁም ሌሎችን ለማረም እንደሚረዳ አስገንዝበው ኤዲት የሚደረግበት የጊዜ ገደብ፣ ግልጸኝነትና ቁጥጥር ወሳኝ መሆናቸውንና አገልግሎቱ ላልተገባ ዓላማ እንዳይውል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ይህም ጊዜ እንደሚወስድና የሙከራ ስራው ከወራት በኋላ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆነው ኤሎን መስክ ከቀናት በፊት 9.2% የትዊተርን ድርሻ መግዛቱ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም የድርጅቱ ከፍተኛ ባለድርሻና የዳሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኗል። መስክ ትዊተርን ጨምሮ ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን በተደጋጋሚ በመተቸትና አስተያየት በመስጠት የሚታወቅ ሲሆን ከአንድ ቀን በፊት “ትዊተር የኤዲቲንግ አገልግሎት ይጀምር ወይ?’’ የሚለውን ጥያቄ ለተከታዮቹ አቅርቦ ነበር።

የትዊተር ኮሚኒኬሽን ቡድን ግን የአገልግሎቱ መጀመር ከመስክ ጥያቄ ጋር ግንኙነት እንደሌለው አስታውቋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::