ለፈተና ደህንነት ሲባል ከዛሬ ጀምሮ ኢንተርኔት ይቋረጣል

ለፈተና ደህንነት ሲባል ከዛሬ ጀምሮ ኢንተርኔት ይቋረጣል የሚል መረጃ እየተሰራጨ ይገኛል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ምን ይላሉ?

ከዛሬ የካቲት 29 ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና መሰጠት ይጀምራል። አምና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሳይሰጥ ወደ ዘንድሮ የተላለፈው ይህ የፈተና አሰጣጥ ዝግጅትም እንደተጠናቀቀ ተሰምቷል።

ከዚህ ጋር ተያያዞ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተንታኞች፣ ፀሀፊዎች እና የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ለፈተናው ደህንነት ሲባል (የፈተና መሰረቅን ለመከላከል) ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ኢንተርኔት እንደሚቋረጥ እየፃፉ ይገኛሉ። አንዳንድ አለም አቀፍ ድርጅቶችም ለሰራተኞቻቸው ይህንን በኢሜይል አሳውቀዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ዙርያ የሚመለከታቸው አካላትን አነጋግሯል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው:

“ፈተና ለመስጠት የግድ ኢንተርኔት መዘጋት አለበት የሚል አሰራር እንዳለ ተደርጎ መታሰቡ ከየት የመጣ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ስለዚህ ፈተና ለመስጠት ሲባል ኢንተርኔት ለመዝጋት የተያዘ እቅድ የለም፣ ኢንተርኔት እየዘጉ ፈተና የመስጫ ግዜ ድሮ አልፏል።”

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ:

“እኔ የከፍተኛ ትምህርት እንጂ የ12 ክፍል ፈተና ባይመለከተኝም እንዲህ አይነት [ኢንተርኔት የመዝጋት] እቅድ እንዳለ እስካሁን አላውቅም።”

የኢትዮ ቴሌኮም የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ:

“በዚህ ዙርያ የደረሰን መረጃ የለም።”

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::