ይህን ያውቁ ኖሯል?  

በመራጮች ምዝገባ ወቅት የተመዘገቡ ዜጎች በቦርዱ በተወሰነው የድምፅ መስጫ ቀን የተመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፅ ይሰጣሉ፡፡  የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚከተለውን ይመስላል: 

• የድምፅ መስጠት ሂደት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይጀመራል፡፡ 

• በዕለቱም መራጮች በምርጫ ጣቢያው ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ እከስ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ በመገኘት ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ፡፡ በነዚህ ሰዓታት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ያልተቋረጠ የድምፅ መስጠት ተግባር ይከናወናል፡፡ 

• ማንኛውም መራጭ ዜጋ በምርጫ ጣቢያው በአካል በመገኘት በሙሉ ነፃነት ድምፅ ይሰጣል፡፡  

• ማንኛውም ዜጋ ድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ ከሚመርጠው እጩ አጠገብ ባለው ቦታ ማንኛውንም (ኤክስ፣ ራይት ወይም የጣት አሻራ) ምልክት በማድረግ ድምፁን ይሰጣል፡፡  

• ማንኛውም ድምፅ የሚሰጠው በሚስጥር ነው፡፡ ድምፅ ለመስጠት እገዛ የሚያስፈልጋቸው ድምፅ ሰጪ ዜጎች ድጋፍ የሚሰጣቸውን ሰው ይዘው የሚስጥር ድምፅ መስጫ ውስጥ መገኘት ይችላሉ፡፡ ድጋፍ ሰጪው መብቱ በህግ ያልተገደበ መሆን አለበት፡፡  

ማንኛውም መራጭ ድምፅ መስጠት የሚችለው: 

• በመራጭነት በተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ ላይ፣ 

• የመራጮች መታወቂያ ካርድ ሲኖረው፣ 

• በመራጮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሲገኝ፣ 

• እንዲሁም ድምፅ ያልሰጠ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ 

• ማንኛውም መራጭ ድምፅ ለመስጠት በተገኘበት ምርጫ ጣቢያ ላይ ይዞ የተገኘውን የማንነት መግለጫ ሰነዶች በጣቢያው ላይ በሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ድምፅ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን ማጣራት ይችላሉ፡፡  

• አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን፣ ህጻናትን የያዙ ወላጆች እና ነፍሰ ጡሮች በምዝገባም ሆነ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ 

ድምፅ የተሰጠባቸው ወረቀቶች ከሚከተሉት በአንዱ ምክንያት ዋጋ አልባ ሊሆኑ ይችላሉ: 

• የመራጩ ማንነት በስም የተገለፀ ከሆነ፣ 

• ለምክር ቤቱ መምረጥ ከሚቻለው እጩዎች ቁጥር በላይ ምልክት የተደረገበት ከሆነ፣ 

• መራጩ ማንን እንደመረጠ መለየት የሚያስቸግር ከሆነ፣ 

• ሕጋዊ የድምፅ መስጫ ወረቀት ያልሆነ ወይም በምርጫ ጣቢያው ያልተሰራጨ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሆኖ ከተገኘ፡፡ 

ምንጭ: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::