የኢትዮጵያ ኢ-ቪዛ (E-Visa) እና በመዳረሻ በሚሰጥ ቪዛ (Visa on Arrival) አገልግሎት ቆሟል? 

በርካቶች ከትናንት ጀምሮ በ E-Visa እና Visa on Arrival ዙርያ አዲስ መመርያ ወጥቷል፣ ሌሎቹ ደግሞ በኢሚግሬሽን ድረ-ገፅ እድሳት ምክንያት ቆሟል መባሉን እንደሰሙ፣ ማረጋገጫ ግን እንዳላገኙ መረጃ አድርሰውናል። 

ኢትዮጵያ ቼክ መረጃዎችን ለማግኘት የኢሚግሬሽን ቢሮን እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረ-ገፆችን ተመልክቷል፣ እንዲሁም ኢሚግኤሽንን አናግሯል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትናንት ምሽት በድረ-ገፁ ላይ እንዳሰፈረው ከኢሚግሬሽን ቢሮ በመጣ መመርያ መሰረት የ E-Visa እና Visa on Arrival አገልግሎቶች ከአርብ እኩለ-ለሊት ጀምሮ ለግዜው አይሰጡም። ይህ ግን የትራንዚት መንገደኞችን እንደማይመለከት አክሎ ገልጿል፣ ይህን መልዕክቱን ግን ቆየት ብሎ ከገፁ ላይ አንስቷል። 

የኢሚግሬሽን ድረ-ገፅ ላይ እንደተመለከትነው ደግሞ የ E-Visa ድረ-ገፁ እድሳት ላይ እንዳለ ገልፆ ተገልጋዮች ለቪዛ ጉዳዮች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ኤምባሲ ወይም ቆንፅላ ቢሮ እንዲያመሩ ይመክራል። 

በዚህ ዙርያ ኢሚግሬሽን ለኢትዮጵያ ቼክ ዛሬ ጠዋት ባደረሰው መረጃ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት ተቋሙ እንዳለው አገልግሎቱ የተቋረጠው  በድረ-ገጹ ላይ የማሻሻያ ስራ እየተከናወነ በመሆኑ ነው። የማሻሻያ ስራው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅም አክሎ ገልጿል። 

በዚህም መሰረት የ E-Visa ያላቸው እንዲሁም Visa on Arrival የሚፈልጉ ተጓዦች ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ የአየር ጉዞን ማድረግ አይችሉም፣ አየር መንገዶችም አያሳፍሩም። ይህም ማለት ፓስፖርት፣ ቢጫ ካርድ (የትውልደ ኢትዮጵያዊ ካርድ) እና የተለጠፈ ቪዛ ያላቸው ብቻ መጓዝ ይችላሉ። ጉዳዩ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ወደ ኢትዮጵያ በረራ የሚያደርጉ አየር መንገዶችን ይመለከታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::