የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት:- አሉባልታዎች እና እውነታው!

በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ–19 በሽታ አምጭ የሆነው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ አየተሰራጨ ይገኛል። ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም ከ247,000 በላይ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር መረጃዎች ያሳያሉ።

ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ክትባቶች በተለያዩ መድሃኒት አምራች ኩባን ያዎች ተመርተው በመላው አለም በመሰራጨት ላይ የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያም ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት በየካቲት ወር መጨረሻ ተረክባለች። ክትባቱም ከመጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች በሚገኙ የጤና ተቋማት መሰጠት ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር ዳንኤል ለኢትዮጵያ ቼክ እንደገለጹት ክትባቱ መሰጠት ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ከ1,000 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ700,000 በላይ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ወስደዋል። ክትባቱን ለመውሰድ ይበልጥ ተጋላጭ ተብለው የተለዩ ዜጎች ቅድሚያ የተሰጣቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል የሕክምና ባለሙያዎች፣ የኮቪድ 19 አስተባባሪ ግብረኃይል አባላት እና ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ እና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ዜጎች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች ይገኙበታል፡፡

ነገር ግን በክትባቱ ዙሪያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የሴራ ትርክቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ስጋቶችን በመፍጠራቸው ምክንያት ዜጎች ክትባቱን ለመውሰድ እንዲያመነቱ ስለማድረጉ የሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጧል። ለዚህም እንደ አንድ ምክንያት የሚነሳው በህብረተሰቡ ውስጥ ስለክትባት ምንነት ያለው መረዳት አናሳ መሆኑ ይጠቀሳል። ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ አድርጎ መውሰድ እና በነዚህ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎችን እውነት ናቸው ብሎ መቀበል ሌላኛው ምክንያት ነው ብሎ ማቅረብ ይቻላል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ያናገራቸው የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶ/ር ዳንኤል ስለክትባቱ የሚነገሩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመዋጋት ማህበረሰቡን የማንቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አርዕያ የሚሆኑ ግለሰቦች ክትባቱን ሲወስዱ ማሳያት ሚንስቴር መስሪያቤቱ የህብረተሰቡን ንቃት ለማሳደፍ እየተጠቀመባቸው ከሚገኙ ዘዴዎች አንዱ ነው። በሀገሪቱ የሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም እየተከናወነ ያለው የማንቃት ስራ ተጠናክሮ

 እንደሚቀጥልም ሃላፊው ተናግረዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::