ልጆችና ታዳጊዎችም ለሀሰተኛ መረጃ እና ለሴራ ትንተና ተጋላጭ ናቸው፣ ታድያ በዚህ ዙርያ ምን ማወቅ አለብን?

ሀሠተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም የሴራ ትንተናዎች በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተፅኖ ያደርሳል። በተለይ በልጆችና በታዳጊዎች ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽኖ የከፋ ስለመሆኑ በሌሎች ሀገሮች የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ሀሠተኛና የተዛባ መረጃ ልጆችና ታዳጊዎች በነጻ የማሰብና የመመርመር ዝንባሌያቸውን በማቀጨጭ ለነገሮች ያላቸው እይታ ውስን እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። እንዲሁም የሴራ ትንተናዎች ልጆችና ታዳጊዎች የመጠየቅና የመመርመር ጉጉታቸው ላይ ሳንካ በመሆን ለሳይንሳዊ መንገዶች (scientific methods) ባይተዋር እንዲሆኑ እድል ሊፈጥር ይችላል።

ልጆችና ታዳጊዎች ለሀሠተኛና ለተዛባ መረጃ እንዲሁም ለሴራ ትንተና ከሚያጋልጧቸው መንገዶች መካከል በወላጆቻቸው እውቅና እና እውቅና ውጭ በሚጠቀሟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ኮምፒዩተሮች የሚያገኟቸው መተግበሪያዎችና ድረ-ገጾች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

በልጆችና በታዳጊዎች የማሰብ፣ የመጠየቅ፣ የመርመር እንዲሁም እውነትን የማወቅ ነጻነት ላይ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች እንዲሁም የሴራ ትንተናዎች እክል እንዳይፈጡ ወላጆች ከፍተኛ ሀላፊነት አለባቸው። ለዚህም ከልጆችና ከታዳጊዎች ጋር መረጃንና የመረጃ ማግኛ ዘዴዎችን በተመለከተ ቀጣይነት ያለውና ግልጽ መስተጋብር መፍጠር ግድ ይላቸዋል።

1. ልጆችና ታዳጊዎች የትኞችን መተግበሪያዎችና ድረ-ገጾች አብዝተው እንደሚጠቀሙ መከታተል። ይህም ወላጆች ልጆቻቸው ለምን አይነት መረጃ እየተጋለጡ መሆኑን እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።

2. ሀሠተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም የሴራ ትንተና መኖሩን ማሳወቅ። ሀሠተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም የሴራ ትንተና በነባራዊው አለም እያስከተለ ያለውን ጉዳት ምሳሌዎችን በመስጠት ማስረዳት።

3. ከልጆችና ታዳጊዎች ጋር ስለ መረጃ በግልጽና ቀጣይነት ባለው መንገድ መወያየት። ለምሳሌ በእውነታና በአስተያየት መካከል ስላለው ልዩነት ማስረዳት ወይም ቀለል ያሉ ምሳሌዎችን በማንሳት ሠተኛና የተዛባ መረጃ እንዲለዩ በማድረግ ሊሆን ይችላል።

4. ልጆችና ታዳጊዎች ስለሰሟቸው መረጃዎች መጠየቅ እንዲሁም መረጃዎችን እንዲገመግሙ ማበረታታት። በግምገማቸው ላይ ተመርኩዞ ምክንያታዊ ውይይት ማድረግ።

5. ልጆችና ታዳጊዎች የሚጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች አሰራር ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ። ለምሳሌ አንዳንድ ፕላትፎርሞች ላይ የሚሰጧቸውን መውደዶች (Like) ተመርኩዘው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ነገሮች እንድንመለከት እንደሚጋብዙ ሊሆን ይችላል።

ልጆችንና ታዳጊዎችን ስለመረጃ በማስተማር እውነትን ከሀሠት፣ ሳይንስን ከሴራ የሚለይ ትውልድ እንፍጠር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::