የምርጫ ጣቢያዎች ከ1500 በላይ ሰው መመዝግብ ይችላሉ?

አንዳንድ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች የምርጫ ጣቢያዎች “የተፈቀደልንን ሰው መዝግበን ጨርሰናል” የሚሉ ጽሁፎችን ለጥፈው ማየታቸውን ይህም ጥያቄ እንዳጫረባቸው ሲገልጹ ኢትዮጵያ ቼክ ተመልክቷል።

ለምሳሌ ሀብታሙ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ‘የእናት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የውይይት መድረክ’ በተባለና ከ12 ሺህ በላይ አባላት ባሉት የፌስቡክ ቡድን የሚከተለው ጥያቄ አዘል መልዕክት ጽፏል:-

“የእጩዎች ምዝገባ፣ በምርጫ ጣቢያ ለምን አንድ ሺ አምስት መቶ (1500) ሰው ብቻ ተመዝግቦ ካርድ እንዲወስድ ተደረገ!? በክፍለ ሀገርም በአዲስ አበባም ባሉ አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን፣ በውስጥ መሥመር በደረሰኝ መረጃ መሠረት፣ ምርጫ ጣቢያው ኮታችንን ሞልተናል ብሎ በር ዘግቶ እየመለሳቸው እንደሆነ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ምን ለማለት ተፈልጎ ነው እንዲህ የተደረገው!?”

ኢትዮጵያ ቼክ የጉዳዩን ህጋዊነት ለማጣራት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የስነምግባር አዋጅ 1162/2011ን ተመልክቷል። የአዋጁ አንቀጽ 15 ቁጥር 6 “እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ብዛት ከ1500 መብለጥ የለበትም” ይላል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከሶስት ቀናት በፊት ጉዳዩን በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ፣ በየአንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚመዘገቡ የመራጮች ቁጥር ከ1500 መብለጥ እንደሌለበት የተደነገገው በድምጽ መስጫ ቀን የሰው መጨናነቅንና የዜጎች የመምረጥ መብትን ለማረጋገጥ በማለም መሆኑን ገልጿል።

ቦርዱ በሰጠው ማብራሪያ በአንድ የምጫ ጣቢያ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 1500 ሲሞላ የሚወሰዱ እርምጃዎችንም ጠቁሟል። ከሚወሰዱ እርምጃዎች አንዱ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች በተመሳሳይ ምርጫ ክልል እና በቅርብ ርቀት ያሉ የምርጫ ጣቢያዎችን በማጣራት መራጮች ካርድ የሚያገኙበትን ቦታ መጠቆም ይሆናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::